የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት ቤተሰቦች በቀበና ወንዝ ዳርቻ የኮሪደር ልማት የእግር ጉዞ አካሄዱ

AMN- ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት ቤተሰቦች በቀበና ወንዝ ዳርቻ በተገነባው አዲስ የኮሪደር ልማት ስፍራ ስፖርታዊ የእግር ጉዞ አካሄዱ

የመርሃ ግብሩ ዓላማ አዲስ የተገነባውን የቀበና ወንዝ ዳርቻ የኮሪደር ልማት ለህብረተሰቡና ለተለያዩ የስፖርት ቤተሰቦች አስተዋውቆ የበለጠ ተደራሽ ማድረግ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት ተሳትፎ ዳይሬክተር እንግዳወርቅ ዳንኤል፤ የእግር ጉዞ መርሃ ግብሩ የስፖርት ቤተሰቡን አንድነት ከማጠናከሩ ባሻገር የአካላዊና አእምሮአዊ ጤንነትን ለመጠበቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የስፖርት ቤተሰቦች እነዚህን መሰል አዳዲስ የልማት መዳረሻዎች በመጠቀም ስፖርታዊ ውድድሮችን ማካሄድ እንደሚችሉ በመግለጽ የወንዝ ዳርቻዎች ለስፖርት ቱሪዝሙ ትልቅ ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በጉዞው ላይ የተሳተፉት የቴኳንዶ አትሌቶችና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት በበኩላቸው፤ በቀበና ወንዝ ዳርቻ በተደረገው ጉዞ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

የተከናወነው የልማት ሥራ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመስጠቱም በላይ ለስፖርተኞች ውብ የልምምድና የመዝናኛ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቢሮው የቀበና ፕሮጀክትን ለማስተዋወቅ የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም መገለጹን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

በመርሐ ግብሩ ማስተሮች፣ አሰልጣኞች፣ የስፖርተኛ ቤተሰቦች እና የስፖርት አፍቃሪያን የተገኙ ሲሆን የእነዚህ ውብና ጽዱ ስፍራዎች ህልውና እና ዘላቂነት የሚወሰነው በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን በስፖርቱ ቤተሰብም ባለቤትነት ስሜት መሆኑን ተመላክቷል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review