AMN- ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም
የአራዳ ፓርክ የጉስቁልና ታሪክን፣ የቆሻሻና የብክለት ስጋትን እንዲሁም የአስከፊ ድህነትን ገጽታ የቀየርንበት ታላቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፣ የባዕዳንን አሉታዊ የታሪክ አሻራዎች በመናድ፣ የኢትዮጵያን ውበትና የትውልድን አዲስ ታሪክ በጋራ በማተም አዲሱን ማንነታችንን ገንብተናል ብለዋል።
ከፒያሳ አካባቢ የተነሱ ነዋሪዎቻችንን ለሰው ልጅ ክብር ከማይመጥኑና ከተጎሳቆሉ መኖሪያዎች አውጥተን፤ እጅግ ጤናማ፣ ነፋሻማና ሰብአዊ ክብርን የሚመጥን መሰረተ ልማት የተሟላለት መኖሪያ “ቤት ለእምቦሳ” ብለን አስረክበናል።

ማህበራዊ መስተጋብራቸው ሳይቋረጥ እድርና እቁባቸውን ጠብቀው በጋራ እንዲኖሩም አድርገናል። ፒያሳን መልሰን ስንገነባ እውነተኛ ስልጣኔንና አራድነትን በሚያሳይ መልኩ ነው።
ወንዞቻችን ከቆሻሻና ከበሽታ አምጪነት ተላቀው ዛሬ የቱሪስት መዳረሻ፣ የተፈጥሮ ውበት መገለጫና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሆነዋል።
የአራዳ ፓርክ በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ የተቀናጀ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት ማዕከል ሲሆን፣ በውስጡ የሚከተሉትን ዋና ዋና አገልግሎቶች ይዟል፦
1. የትራንስፖርትና የመንገድ መሰረተ ልማቶች
• የአስፓልት መንገድ፦ 5 ኪ.ሜ. የሚረዝም የውስጥ ለውስጥ መንገድ።
• የእግረኛ መንገድ፦ 6 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ምቹ የእግር ጉዞ መስመር።
• የብስክሌት መስመር፦ 5 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው የሳይክል ሌን።
• የመሮጫ ትራክ፦ 5 ኪ.ሜ. የሚረዝም ለስፖርተኞች የተዘጋጀ መስመር።
2. የንግድና የፋይናንስ አገልግሎቶች
• የንግድ ሱቆች፦ ከፒያሳ ለተነሱ ነጋዴዎች ቅድሚያ የተሰጠባቸው 131 ዘመናዊ ሱቆች።
• ምግብና መጠጥ፦ 7 ካፌዎችና ሬስቶራንቶች።
• ግብይትና ባንክ፦ 1 ትልቅ ሱፐርማርኬት እና 1 የባንክ ቅርንጫፍ።
3. የስፖርት፣ የኪነ-ጥበብና የመዝናኛ መገልገያዎች

• ዘመናዊ የስፖርት አሬና፦ አንድ (1) ዘመናዊ የአካል ብቃት ማዕከል (Gym) እና 7 አዳራሾች።
• መድረኮች፦ 8 ፕላዛዎችና 3 አንፊ-ቴአትሮች (ለተለያዩ ኩነቶች ማዘጋጃ የሚውሉ)።
• ልዩ ውበት፦ በአይነቱ ልዩ የሆነ “ዳንሲንግ ፋውንቴን” (ተንቀሳቃሽ ፏፏቴ)።
• ብሔራዊ ምልክት፦ በሀገራችን ረጅሙ የሆነው ባለ 100 ሜትር የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ መስቀያ።
4. ለሕፃናትና ለቤተሰብ
• የሕፃናት መጫወቻ፦ 4 በሚገባ የተሟሉ ዘመናዊ የመጫወቻ ስፍራዎች።
• ትንሿ ከተማ፦ ሕፃናት ስለ ሀገራቸው እውቀት የሚቀስሙበትና የሚዝናኑበት ልዩ ስፍራ።

5. የተፈጥሮ ልማትና የንፅህና አገልግሎቶች
• አረንጓዴ ልማት፦ 15 ሄክታር መሬት በሳርና በተክሎች የተሸፈነ፣ በፓርኩ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ 22 የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች።
• ፓርኪንግ፦ በአንድ ጊዜ 280 መኪናዎችን መያዝ የሚችል ሰፊ ማቆሚያ ወዘተ አገልግሎቶችን አካትቷል።
የአራዳ ፓርክ የመሬት አጠቃቀምን በላቀ ደረጃ ጥቅም ላይ ያዋለ ፕሮጀክት ነው።

መሬትን ከስር ለሱቅና ለአዳራሽ፣ ከላይ ደግሞ ለፕላዛ በመጠቀም ውስን የሆነውን የከተማ መሬት በብቃት ተጠቅመናል።
በተጨማሪም በአካባቢው የነበሩ ከ700 በላይ ቤቶችና ሕንፃዎች ታሪካዊ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲታደሱ ተደርጓል።
ይህ ፓርክ ከንግድ እስከ ስፖርት፣ ከቤተሰብ መዝናኛ እስከ ዓለም አቀፍ የኪነ-ጥበብ መድረኮችን አጣምሮ የያዘ የከተማዋ አዲስ የቱሪስት መዳረሻ ነው።
እንኳን ደስ አለን!