AMN- ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ እያሳየችው ያለው ፈጣን ለውጥ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የማንሰራራት ጉዞ እና የብልጽግና አቅጣጫ በግልጽ የሚያሳዩ ነጸብራቆች መገኛ ሆናለች።
የኮሪደር ልማት እና ዘመናዊ የከተማ መዋቅር፣ የአረንጓዴ ልማት ፣የዲጂታል አስተዳደር እና የህዝብ አገልግሎት መስፋፋት፣የስራ ፈጠራ እና የወጣቶች ማብቃት፣ አለም አቀፍ ዝግጅቶች እና የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ስኬቶች ከተማዋ የኢትዮጵያ የዕመርታና የዕድገት ምዕራፍ ግንባር ቀደም መገለጫ መሆኗን ማሳያዎች ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለፉት ጥቂት ዓመታት ተግባራዊ ያደረጋቸው ግዙፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከመሰረቱ የቀየሩ፣ምቹ እና ንጹህ መንገዶችን፣ የእግረኛ መተላለፊያዎችን፣ አረንጓዴ ቦታዎችን እና የመዝናኛ ፓርኮችን በማቀናጀት ለኑሮና ለስራ ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ተፈጥረዋል።
መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ የትራፊክ ፍሰትን የሚያቀሉ፣ የከተማዋን ውበት የሚጨምሩ እና የነዋሪዎችን ማህበራዊ ህይወት የሚያሻሽሉ ዘመናዊ መዋቅሮች ተገንብተዋል።
አዲስ አበባ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማዕከል በመሆን ለሀገሪቱ የኢኮሎጂ ማገገም ዘመቻ ትልቅ አርአያ ሆናለች።
ይህም፣ ከተማዋን ውብ እና ጤናማ ለማድረግ የተከናወኑ የከተማ ግብርና፣ መናፈሻዎች እና የንጹህ ወንዝ ዳርቻ ልማቶች ለነዋሪዎች ንጹህ አየር ከመስጠት ባለፈ፣ የከተማዋን ስነ-ምህዳር ጠብቆ ለማቆየት ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

የዲጂታል አስተዳደር እና የህዝብ አገልግሎት መስፋፋት ደግሞ፤ በፌዴራል ደረጃ የተጀመሩ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራዎች ማሳያ በሆነ መልኩ፣ አዲስ አበባ የዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥ ግንባር ቀደም አድራጊ ሆናለች።
እንደ “አዲስ መሶብ” ያሉ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ፖርታሎች እና ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ አሰራሮች የህዝብ አገልግሎቶችን ፈጣን፣ ግልጽ እና ከቢሮክራሲያዊ ማነቆዎች የጸዱ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል።
የአለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና የመስተንግዶ ተቋማት መስፋፋት የቱሪዝም መነቃቃት እና የኮንፈረንስ ቱሪዝምን እያፋፋው ይገኛል።
በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ለወጣቶች ሰፊ የስራ ፈጠራ እድሎችን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
በተለይ በኮሪደር ልማት እና በዘመናዊ ገበያ ማዕከላት ግንባታ ሂደት ወጣቶች እና ሴቶች በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ በባለቤትነት እንዲሳተፉ ሰፊ ዕድሎች ተመቻችተዋል።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ በተግባር የሚታይበት መስታወት ሆኗ በተምሳሌትነት እየገሰገሰች ትገኛለች።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ