AMN- ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም

በ2018 የትምህርት ዘመን ከእቴጌ መነን የልጃገረዶች 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ለሕክምና ትምህርት መዘጋጀቷን ተማሪ ኤፍራታ አለማየሁ ገለጸች።
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ውጤት ይፋ እየሆነ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ከእቴጌ መነን አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የተፈጥሮ ሳይንስ ሥርዓተ ትምህርት ስትከታተል የነበረችው ተማሪ ኤፍራታ አለማየሁ አስደናቂ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጻለች።
ተማሪ ኤፍራታ አለማየሁ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና 574.84 ነጥብ በማምጣት በከፍተኛ ውጤት ማጠናቀቋ ይታወቃል።
ተማሪዋ ለዚህ ስኬቷ በዋነኝነት የፈጣሪዋ እገዛና ጸሎት ዋነኛው ምስጢር መሆኑን የገለጸች ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ በየቀኑ ለሚገጥሟት ፈተናዎች እጅ ባለመስጠት እና ፈተናዎችን በትዕግስት በመሻገር በየቀኑ ያለማቋረጥ በትጋት ከተጠና ውጤታማ የማይሆንበት መንገድ እንደሌለ ጠቁማለች።
በተጨማሪም ለራሳችን መስራት እንደምንችል እና ያለንን አቅም በማመን እና በራስ የመተማመን ስሜት ማጥናቷ ለውጤቱ መመዝገብ መሰረት እንደሆናት ተናግራለች።
በተቻላት አቅም ያልገቧትን ጥያቄዎች በመጠየቅ፣ የክፍል ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ እና አስተማሪዎች ጥያቄዎችን ሲጠይቁ በንቃት እንደምትሳተፍ የምትናገረው ተማሪ ኤፍራታ፣ አብዛኛውን የትምህርቷን ርዕስ በክፍል ውስጥ አጠናቅቃ እንደምትወጣ ገልጻለች።
በክፍል ውስጥ ትምህርታቸውን በትኩረት ከሚከታተሉ ተማሪዎች መካከል እንደምትጠቀስ የገለጸችው ተማሪዋ፣ ይህም ለፈተና ዝግጅት ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላት አብራርታለች። እንዲሁም በማንበብ ሂደት ውስጥ ማስታወሻ መያዝ እጅግ ጠቃሚ ነገር መሆኑን እና ይህም በፈተና ወቅት ከፍተኛ በራስ መተማመን እንደሚፈጥርላት ተናግራለች።
እቅዷ ከ580 በላይ ውጤት ማምጣት እንደነበር ለኤ ኤም ኤን የገለጸችው ተማሪ ኤፍራታ፣ በፈተናው ወቅት የነበሩትን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት “በቃ 570 ካመጣሁ ይበቃኛል” ብላ እንደነበርም አንስታለች።
ለዚህ ድል ስኬት ከፈጣሪዋ በመቀጠል የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ማህበረሰብ፣ መምህራን እና የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ሰራተኞች ድጋፍ የላቀ እንደነበር ተማሪዋ አስገንዝባለች።
ተማሪዋ አራት ዓመት ሙሉ ከጎበዝ ተማሪዎች ጋር መማሯን እና የመምህራንም ሁለገብ ድጋፍ ትልቅ መነቃቃትን እንደፈጠረላት ገልጻለች።
አያቷ የፊዚክስ ትምህርት መምህር እንደነበሩ ያነሳችው ተማሪ ኤፍራታ ከልጅነቷ ጀምሮ ላደረጉላት ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ ምስጋና አቅርባለች።
ሀገራችን አሁን ላይ በርካታ የተማረ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደምትፈልግ የጠቆመችው ተማሪ ኤፍራታ፣ በዲጂታሉ ዘመን ለሚከሰቱ ችግሮች ተግባራዊ መፍትሄዎችን በማምጣት የህክምናውን ዘርፍ የመቀላቀል ትልቅ እቅድ እንዳላት ጠቁማለች።
በወርቅነህ አቢዮ