የከተሞቻችን ማንሠራራት፥ የሀገራችን ማንሠራራት መልክ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN – ጳጉሜን 2/2018 ዓ.ም

የከተሞቻችን ማንሠራራት፥ የሀገራችን ማንሠራራት መልክ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ከተሞች የሥልጣኔ መስታወቶች ናቸው ፤ የሀገርን የዕድገት ደረጃ፣ የሕዝቦችን የአስተሳሰብ ከፍታ፣ የአካባቢ ጥበቃ ቁርጠኝነትና የልማት አቅጣጫ በግልጽ የሚያሳዩ ሕያው ገጾች ናቸው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ መላ የኢትዮጵያ ከተሞች ያንሠራራው የኮሪደር ልማት ሥራም ይህንኑ እውነታ በተጨባጭ እያሳየ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

ከአዲስ አበባ እስከ ባሕር ዳር ፣ ከጂማ እስከ ሐረር፣ ከድሬዳዋ እስከ ጅግጅጋ፣ ከሐዋሳ እስከ አዳማ፣ ከጎንደር እስከ ቢሾፍቱ፣ ከአርባምንጭ እስከ ነቀምት፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ፣ ከሆሳዕና እስከ ሰመራ፣ ከሶዶ እስከ ደሴ፣ ከቦንጋ እስከ ዲላ እና ሌሎችም ከተሞች ገጽታው እየተቀየረ፣ መልካቸው እያማረ ነው ብለዋል።

ይህ ለውጥ የመንገድ መስፋት ወይም የአካባቢ መዋብ ብቻ አይደለም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፣ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ አረንጓዴ ስፍራዎችና ዘመናዊ የመሠረተ ልማት አውታሮች ከተሞችን ይበልጥ ለኑሮ፣ ለሥራና ለመዝናናት ምቹ እያደረጓቸው ይገኛሉ ብለዋል።

ከዚህም በላይ የከተማ ልማት ማለት ለጥቂቶች የተመቸ ከተማ መፍጠር ሳይሆን ለሁሉም ዜጎች የሚደርስ አካታች ከተማ መገንባት መሆኑ በተጨባጭ ታይቷል ሲሉ የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ፣ በከተሞቻችን ለሕፃናት፣ ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ ከተማ መፍጠር የልማት ዋነኛ መለኪያ ሆኗል ብለዋል።

በዚህ ሂደት የከተሞቻችን ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች እየተጠበቁ፣ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ አዲስ ገጽታም እየተላበሱ ነው። የትናንቱን ታሪክ ከነገ ራዕያችን ጋር የሚያገናኙ ከተሞች እየተገነቡ የመሰረተ ልማትና የቱሪስት እንክብካቤ ተደርጎላቸው ለአለም አቀፍ ጎብኚዎች ይበልጥ ምቹና ሳቢ ሆነዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ዛሬ የምናያቸው የተለወጡ ከተሞች ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ የምንገነባት የበለፀገች ኢትዮጵያ አዲስ ገጽ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያም በተግባር እያንሠራራች ነው ሲሉ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፣ ከተሞቻችን ሲለወጡ፣ የሀገራችን ገጽታ ይለወጣል ፤ የሕዝባችን ኑሮ ሲሻሻል፣ የሀገራችን ከፍታ ይጨምራል ፤ ለዚህ ስኬት በላቀ ትጋት እንሠራለን ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review