AMN ጳጉሜን 3/2018
የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት የጽናት ቀንን በተለያዩ መርሐ ግብሮች እያከበሩ ይገኛሉ።
ቀኑ “ጽናት የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሐሳብ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ሲሆን፤ የመከላከያ ሠራዊት፣የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እንዲሁም የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ሥራዎች በመድረኩ ይዘከራሉ።
ተቋማቱ ለሀገር ማንሰራራት በየዘርፉ እያከናወኑት ላለው ሥራ እውቅና መስጠት እና ቀጣይ ተልዕኮዎችን በላቀ ደረጃ ማስቀጠል ቀኑ የሚከበርበት ዋነኛ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ የተቋማቱ ሚና፣ እየተገኙ ያሉ ውጤቶች እና ተሞክሮዎች በመድረኩ የሚዳሰሱ ይሆናል።
በተለይም ተቋማቱ በሀገር ግንባታ ሂደት፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር፣ ሰላምን በማጽናት እና የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር ዙሪያ ያከናወኗቸው አንጸባራቂ ሥራዎች ይወሳሉ።
በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ እንዲሁም ከፍተኛ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት አመራር አባላት ተገኝተዋል።