AMN – ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን እንዲሆን በሚዲያ ሥራዎቹ ላበረከተው በጣም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እውቅና ተሰቶታል።
በሸራተን አዲስ በተካሄደው የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር ላይ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ሰለሞን ዲባባ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የእውቅና የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።
ተቋሙ በሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ የተገነባው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለስኬት እንዲበቃ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮቹ አማካኝነት ያከናወናቸው አበይት ሥራዎች ዋጋ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ወቅታዊ፣ ጥራት ያላቸውና ፈጠራ የታከለባቸው ይዘቶችን በማቅረብ ረገድ አርአያ መሆኑም ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተገለጸው፤ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዜጎች የጋራ ትልማቸውን በአንድነት እንዲያሳኩ በማስተባበር ረገድ የድርሻውን እየተወጣ የሚገኝ ተወዳዳሪ ሚዲያ ነው።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በወቅቱ እንደገለጹት፣ ግድቡ ለፍሬ እንዲበቃ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ በጉልህ የሚታወስ ነው።
በዕለቱ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለግድቡ ስኬት ላደረገው ያልተቋረጠ አስተዋጽኦ እውቅና የተሰጠው ሲሆን፤ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በደሴ ብርሃኑ