AMN – ጳጉሜን 3/ 2018 ዓ.ም
ዘመኑ በሀገራት ላይ የቀጥታ ተኩስ የሚከፈትበት አይደለም ይልቁንስ ጠላትን በቴክኖሎጅ አቅም በልጦ አቅምን የማሽመድመድ አካሂያዶች በዉል የሚታዩበት እንጅ፡፡
ከግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት የሳይበር ጥቃት እስከ ሰላም እና ፀጥታ ተቋማት ሚስጥራዊ መረጃ ምንተፋ ከሀገር መሰረተ ልማቶች ጥቃት እስከ መገናኛ ብዙሀን የግንኙነት መስመር ጠለፋ ድረስ የሚሻገሩ የሳይበሩ አለም አዲስ የዉድድር ሜዳ የሀገራት አቅም መፈተኛ ሆነዋል፡፡
ከትናንት በመማር ዛሬ ከአለም ጋር ለመወዳደር ነገ ላይ ደግሞ ካደጉ ሀገራት ጋር የመሰለፍ ራዕይን የሰነቀችዉ ኢትዮጵያ ለራዕዮቿ እዉን መሆን ተቋማትን ገንብታለች፡፡
የኢንፎፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩት ደግሞ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ናቸዉ፡፡
የሀገረን ክብር በፀና መሰረት ላይ ለማቆም “soft Power” ላይ በሚገባ መስራት አስፈላጊ ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ኢትዮጵያም የተቋማቶቿን ደህንነት እና የሳይበር ጥቃቶች ሙከራ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት እየመከተች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ደግሞ በሰዉ ሰራሽ አስተዉሎት ምጥቀት ላይ ለመድረስ እየሰራች ነዉ፡፡
አለምን በዉል በማጤን የሀገራት አካሄድንም ከግምት ዉስጥ በማስገባት ተቋማቱ በብቁ የሰዉ ሀይል የሚዘወሩ ብቁ ሀይልንም የሚፈጥሩ ይሆኑ ዘንድ አድርጋለች ፡፡
ይህ ስትራቴጂካዊ አካሄድ ተቋማቱ በውጤት፣ ሀገር ደግሞ በጽናት እንድትቀጥል አዲስ በር ከፋች ሆኗል።
በተመስገን ይመር