AMN ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፤ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መኖሪያ ነች፡፡
እነዚህ ብሄሮች፤ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በሃገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ዉስጥ ለሃገራቸዉ ነጻነትና ሉዓላዊነት ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸዉን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
ነጭ ወራሪ ሃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመገዳደር ከመጡበት ከአድዋ ጦርነት ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በሃገሪቱ ላይ የተቃጡ አደጋዎችን በጽናትና በጀግንነት በመመከት የነጻነት ቀንዲል መሆናቸዉን ለመላዉ ዓለም አብስረዋል፡፡
እነዚህ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተለያዩ ቋንቋዎች፤ ሃይማኖቶች፤ ባህሎች እና ማንነቶች ያላቸዉ ሲሆኑ በሃገራቸዉ ነጻነትና ሉዓላዊነት ላይም ጠንካራ አቋም ያላቸዉ ህዝቦች መሆናቸዉ ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ላለፉት በርካታ አመታት የሃገሪቱን ህዝቦች በብሄርና በሃይማኖት ከፋፍለዉ አንድነታቸዉን ሊንዱና ሃገራቸዉን ሊያፈርሱ በርካታ ሴራዎችን ሲያሴሩ ኖረዋል፡፡
መላዉ የኢትዮጵያዊያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ግን በተለያዩ አጀንዳዎች አንድነታቸዉን እና ወንድማማችነታቸዉን ሊንዱ የመጡ ታሪካዊ ጠላቶችን በአንድነትና በጀግንነት በመመከት የጽናት ተምሳሌት መሆናቸዉን በድል አረጋግጠዋል፡፡

ከትናንትናዎቹ የአድዋ ጀግኖች እስከ ዛሬዎቹ የተለያዩ የጸጥታ አካላት ድረስ በርካታ የኢትዮጵያ ጀግኖች ለሃገራቸዉ ሉዓላዊነትና ህልዉና ዉድ ሕይወታቸዉን በመክፈል ኢትዮጵያ ለየትኛዉም ጠላት የማትንበረከክ ጽኑ ሃገር መሆኗን በጀግንነት አረጋግጠዋል፡፡
ዛሬም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ተልእኮ በመቀበል የሃገሪቱን ሉዓላዊነት እና ህልዉና አደጋ ላይ ለመጣል፤ ልማትና እድገቷን ለማደናቀፍ ብሎም ወንድማማች ህዝቦችን በብሄርና በሃይማኖት ሽፋን ደም ለማቃባት የሚቋምጡ የጥፋት ሃይሎችን በጽናት በመመከትና በመታገል ለሃገራቸዉ ሰላምና ደህንነት ያላቸዉን ክብር ዳግም በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያዊያን በሃገራቸዉ ሉዓላዊነትና ህልዉና ላይ ከማንም ጋር የማይደራደሩ የጽናት ተምሳሌቶች መሆናቸዉንም በዘመናት ቅብብሎሽ በማስመስከር ላይ ይገኛሉ፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ