AMN – ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ጀግኖች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችና ትጥቆች ባልነበሩበት ዘመን ጦር፤ ጋሻ እና ጎራዴ ታጥቀዉ ጠላትን ድል አድርገዋል፡፡
ረሃብና ጥሙ፣ ብርድና ሃሩሩ፣ ጋራና ቁልቁለቱ ያልበገሯቸው እነዚያ የነፃነት ታጋዮች በፈረስና በባዶ እግሮቻቸው ጭምር ተጉዘው የውጭ ወራሪ ኃይሎችን ድል በማድረግ አይበገሬነታቸውን አስመስክረዋል፡፡
በተለይ በአድዋ ጦርነት ወቅት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እና የሰለጠነ ወታደር ከነበረው የውጭ ወራሪ ኃይል ጋር በጽናት፣ በጀግንነት፣ በቆራጥነት እና በአይበገሬነት ወኔ ያደረጉት ተጋድሎ ለዘመናት ሲዘከር የሚኖር ሕያው ታሪክ ነው፡፡

በዘመናት ሂደት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች የጸጥታ አካላት በዘመናዊ መልክ እስከተደራጁበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ አባት አርበኞች ያሏቸውን የጦር መሣሪያ እና የሰው ኃይል በመጠቀም ሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር ውድ ሕይወታቸውን ከፍለዋል፡፡
ዛሬ ላይ ግን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ሕልውና የሚከበረው የአሁኖቹ ጀግኖች ከአባቶቻቸው በወረሱት ጽናት፣ ወኔ እና በሰለጠነ የሰው ኃይል ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ የጦር መሣሪያ እና በቴክኖሎጂዎች ጭምር ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ በራሷ ዕውቀትና በልጆቿ አቅም የላቀ የቴክኖሎጂ ብቃት ያላቸውን ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ ዘመናዊ የታጠቁ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን፣ ከባድ መሣሪያዎችንና መድፎችን እንዲሁም ተተኳሽ ጥይቶችን በራሷ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ችላለች፡፡
በተለይ ከሀገራዊ ሪፎርሙ ጋር ተያይዞ ሁሉም የጸጥታ አካላት በተለያዩ ዘርፎች ያካበቱት የጸጥታና ደህንነት አቅሞች ሀገሪቱ በራሷ አቅም እንድትቆም አስችሏታል፡፡
የተገነባው አቅም ሕዝቦች ሰላምና ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ጽኑ መሠረት ላይ እንዲቆም ያስቻለ ከመሆኑም በላይ ሀገራዊ ጽናት በተጨባጭ ልማትና በጠንካራ የመጠበቅና የመከላከል አቅም እንዲረጋገጥ አስችሏል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያታጠቀቻቸው ዘመናዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ከመሆናቸውም በላይ የተለያዩ ተልዕኮዎችን በቀላሉ ለመፈጸም የሚያስችሉ ናቸው፡፡
ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ ከባድ መሣሪያዎች፣ መድፎች፣ ተተኳሽ ጥይቶች እና ሌሎች ወታደራዊ ትጥቆችም ቢሆኑ ዘመኑን የዋጁና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር ትልቅ አቅም የፈጠሩ ናቸው፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እንዲሁም የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያን ማንሰራራት እውን ለማድረግ በተለያዩ መስኮች እየሠሩ የሚገኙት ሥራዎችም የሀገሪቱን የጸጥታና ደህንነት አቅም ያጠናከሩና የሀገሪቱን ዘላቂ ብልጽግና ለማጽናት የሚያግዙ ሆነዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ