AMN – ጳጉሜን 3/2018 ዓ/ም

የኢትዮጵያ ብቸኛ ወር የሆነችው የጳጉሜን ቀናት የተለያዩ ሀገራዊ ራዕዮችን በሚያሳዩ ስያሜዎች እየተከበሩ ይገኛሉ።
የዛሬው የጳጉሜን 3 ቀን የጽናት ቀን በሚል ስያሜ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው።
ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት እየተወጣች የኖረች የጀግኖች ሀገር ናት። የጽናት ቀን ትላንትናን እያስታወሱ ዛሬ ላይ ቆሞ ለነገው ማህበራዊና ሀገራዊ ግንባታ ራስን ለማዘጋጀት የሚያስችል ነው።
ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሻገረውን የጽናት አርማ ከፍ አድርገን በመያዝ፣ አሁንም የሚያጋጥሙንን የውጭና የውስጥ ፈተናዎች በኅብረት ለማሸነፍ በጽናት መቆም ይገባል።
ይህ ዕለት የኢትዮጵያን አገራዊ ጽናት፣ የጸጥታ ተቋማትን ዘመናዊ ቁመና እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነት የተከፈለውን የጀግኖች መስዋዕትነት የሚያስታውስ ሲሆን፤ በሰላምና በሁለንተናዊ እድገት መሠረትነት ላይ ትኩረት አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የጸጥታ አካላት በከፍተኛ ዲሲፕሊን፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲሁም በአየር ኃይልና በሳይበር ቴክኖሎጂ ጭምር በመጠናከር የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም ፈጥረዋል።
ሰራዊቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያመጣቸው ያሉት ታላላቅ የዘመናዊነትና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ውጤቶች ሀገሪቱ የብልፅግና ራዕይዋን ለማሳካትና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚያስችል አቅም ፈጥረውለታል።
የሰራዊቱ የቁመና ለውጥ ለሀገሪቱ ሰላም ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለትምህርት፣ ለግብርና እና ለሌሎች ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎች አስተማማኝ መሠረት ሆኖ ቀጥሏል።
የሰራዊቱ ጽናትና የሕዝብ አብሮነት ተደምሮ የትኛውንም አገራዊ ፈተና ማለፍ እንደሚቻል ከዚህ በፊት የተገኙ ድሎች ማሳያዎች ናቸው።
የዛሬው ጽናት የነገዋ የበለጸገች ሀገር መሠረት ስለሆነ፣ የሰላም እና የጸጥታ ዋስትና ሥራዎች ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ በጽናት ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ እየገሰገሰች መሆኗን በድጋሚ ያረጋግጣሉ።
በአስማረ መኮንን