AMN – መስከረም 06/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአዲስ መንፈስና በድምቀት የተከፍተውን አዲሱን የ2019 የትምህርት ዘመን ጀምሯል፡፡
በዚህም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም ተማሪዎች፣ ወላጆች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ለኤ ኤም ኤን አጋርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ እንዳሉት፤ በ2018 ዓ.ም የታዩ ጥቃቅን ክፍተቶች በዘንድሮው ዓመት እንዳይደገሙ ከትምህርት አሰጣር ጋር የተያያዙ የመግባባት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በክረምት ወራትም የማጠናከሪያ ትምህርቶችና የማነቃቂያ ስትራቴጂዎች ሲተገበሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ለመቀበል በሚያስችል መልኩ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ምቹ ሆነው መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም በሁሉም በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በዕለቱ ትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ተስፋ እንደሚደረግና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በተነደፉ ስልቶች ላይ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጸዳለች ሚካኤል በበኩላቸው፣ የትምህርት ዘመኑ መጀመርን ተከትሎ የምገባ ፕሮግራሙ በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ቁርስና ምሳ እንደሚመገቡ ጠቅሰው፣ ይህ ዝግጅት ለአእምሮ እድገት፣ ለጤና እና ለተማሪዎች አቅም ግንባታ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
የጎሮ ቅድመ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ይስሓቅ ታምሩ በሰጡት አስተያየት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የስምንተኛና የስድስተኛ ክፍል ውጤቶች በጥሩ ሁኔታ እየተሻሻሉ መምጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከ6ሺ700 በላይ ተማሪዎች በመማር ላይ እንደሚገኙና የተሻለ ውጤት ለማምጣት አቅደው ወደ ተግባር መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡
ሌላኛዋ መምህርት ራሔል ሰለሞን በበኩሏ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለአስተማሪዎች አሳልፈው በመስጠት ትልቅ እምነት እንደሚጥሉ አንስታ፤ ነገ ሀገርን የሚረከቡ ህፃናትን በትጋት በማስተማር ረገድ የመምህራን ሚና ከፍተኛ መሆኑንና በዛው ልክ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግራለች፡፡
ሌላኛው መምህር አምሳሉ ስብሃት በበኩሉ፣ ተማሪዎች ከባለፈው ዓመት ውጤት ተሻሽለው እንዲመጡ በመነሳሳት፣ ባለፈው የነበረውን አፈጻጸም በማሻሻል የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት፣ ከክረምት እረፍት በኋላ ጓደኞቻቸውንና አስተማሪዎቻቸውን በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡
ተማሪ ያስሚን አብዲ፣ ተማሪ ሄቨን ገብረሓና፣ ናኒዬ ዘለቀ እንዲሁም ኢክራሓም ሸምሱ በሰጡት አስተያየት፤ ዩኒፎርም፣ ደብተር እና መጽሐፍ ተሟልቶላቸው ትምህርት በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው፤ በዘንድሮው የሚኒስትሪ ፈተና የተሻለ ውጤት በማምጣት ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ግብ አስቀምጠው እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ