ለቤት ፈላጊዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያጋሩት ብሥራት

You are currently viewing ለቤት ፈላጊዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያጋሩት ብሥራት

AMN- ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የተለየ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) መካከል መፈረሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

ይህ ታሪካዊ ስምምነት የሀገሪቱን የቤት ልማት እና የፋይናንስ ዘርፍ ወደ አዲስ ደረጃ የሚያሸጋግር ሁነኛ ርምጃ ነው።

ለመሆኑ በ100 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚቋቋመውና ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን እስከ 200 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ የሚያደርግበት ይህ ኩባንያ ምን ፋይዳዎች ይኖሩታል?

ባንኮች አጭር ጊዜ የሚቆዩ የህዝብ ተቀማጭ ገንዘቦችን በመጠቀም የረጅም ጊዜ የቤት መግዣ ብድሮችን ለመስጠት ይቸገራሉ ፣ ምክንያቱም ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠን ስለሚያጋጥማቸው ነው።

አዲሱ የመልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ባንኮች የሰጡትን የቤት ብድር ሰነድ በመግዛት ጥሬ ገንዘብ መልሰው እንዲያገኙ ያደርጋል። ባንኮችም የሰጡትን ብድር መልሰው ፈጣን ፈንድ እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው ለሌሎች ደንበኞች ተጨማሪ የቤት መግዣ ብድር ማቅረብ እንዲችሉ አቅም ይፈጥርላቸዋል።

እስካሁን በነበረው አሰራር የቤት ብድር ማግኘት ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎች የሚችሉት እና የወለድ መጠኑም ከፍተኛ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚቋቋም ያበሰሩት ኩባንያ የብድር ጊዜያት ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ ወደ ረጅም ዓመታት እንዲራዘሙ በማስቻል፣ ወርሃዊ የክፍያ መጠንን በመቀነስ የብድር ክፍያውን በዜጎች አቅም ተመጣጣኝ የሚያደርገው ይሆናል።

ኩባንያው የመካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የቤት ባለቤት የመሆን ህልማቸውን እውን ለማድረግ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በቀጣይ ዓመታት 1.5 ሚሊየን ቤቶች ለማቅረብ እንደሚሰራ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡ ለዚህ ግብ መሳካት ይህ ስምምነት ዋና የፋይናንስ ሞተር ሆኖ ያገለግላል።

በመንግሥት ላይ ብቻ ተጥሎ የነበረውን የቤት ልማት ፋይናንስ የማቅረብ ሸክም በመቀነስ፣ የግል ባንኮች እና አልሚዎች በሰፊው እንዲሳተፉ መንገድ ይከፍታል።

ስምምነቱ ለበርካታ ዓመታት የቤት ባለቤት መሆን ሕልም ሆኖባቸው ለነበሩ አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተስፋን የሚፈነጥቅ ወሳኝ የፖሊሲ ርምጃ ነው፡፡

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review