በትጋትና ጥረት የተወለደ አዲስ የማንሰራራት ንጋት!

You are currently viewing በትጋትና ጥረት የተወለደ አዲስ የማንሰራራት ንጋት!

AMN መስከረም 8/2019

አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ጽዱ፣ ተወዳዳሪና ዘመናዊ እንድትሆን ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ አቅዶ በሰራው ሥራ ዘርፈ ብዙ ለውጦች ተመዝግበዋል።

በከተማዋ የተገነቡት ሜጋ ፕሮጀክቶችና የልማት ኢኒሼቲቮች የህዝቡን የልማትና የተጠቃሚነት ጥያቄ ከመመለስ ባሻገር ከተማዋ እንድታንሰራራ እና ለሌሎች ከተሞች የብልጽግና ፋና ወጊ እንድትሆን አስችሏታል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ከ60 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት የገቡ ሲሆን በ2018 ዓ.ም ብቻ ከ20ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ችለዋል። ይህ በ24/7 የሥራ ባህል የተተገበረው የፕሮጀክት አፈጻጸም ለከተማዋ ማንሰራራት ጉልህ ድርሻ ተጫውቷል።

በከተማዋ ባለፉት አምስት ዓመታት የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ለከተማዋ ዘመናዊነትን ከማላበስ በዘለለ ነዋሪው ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲንቀሳቀስ ምቹ መደላድል ፈጥረዋል። የመንገድ ኔትዎርክ ሽፋንና ጥራትን በማሳደግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንዲሳለጥ አድርጓል።

በከተማዋ ምንም ያልነበሩ የትራንስፖርት ቴርሚናሎችና መኪና ማቆሚያዎች በበርካታ ቦታዎች ተገንብተው ህብረተሰቡን ከእንግልትና ከአደጋ መታደግ ችለዋል።

የነዋሪዎችን አስከፊ አኗኗር ለማሻሻል ታቅዶ የተተገበረው የከተማ ማደስ ሥራም አዲስ አበባ ፈጥና እንድታንሰራራና ባለፉት ጊዜያት “አይቻልም” ተብሎ የተዘጋውን አዲስ አበባን የመለወጥ ውጥን ወደ ተግባር እንዲቀየር አስችሏል። ከተማዋ ለኑሮ ምቹ፣ ለጤና ተስማሚ እንድትሆን ብክለትን ለመቀነስ በተሰራው የአረንጓዴ ልማት ሥራ የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከ2.8 በመቶ ወደ 24 በመቶ አድጓል።

በተጨማሪ ለከተማዋ ጽዳት በተሰጠው ትኩረት አዲስ አበባ ከ10 ጽዱ የአፍሪካ ከተሞች አንዷ መሆን ችላለች።

በአዲስ አበባ የተመዘገቡ የመሰረተ ልማት ስኬቶች ለነዋሪዎቿ ዘመናዊ አገልግሎት ከመስጠታቸው በተጨማሪ ከተማዋን ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት እንድትሸጋገር አስችሏታል።

በኮንፍረንስ ቱሪዝም በ2018 ዓ.ም. ብቻ ከ220 በላይ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችን በማስተናገድ አዲስ አበባ ማንሰራራቷን አስመስክራለች። – የከንቲባ ጽ/ቤት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review