AMN መስከረም 8 ቀን 2019
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዱባይ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት፣ በውጭ ሀገር ተደብቀው ዜጎችን በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙቧቸው በነበሩት እነ ዳውድ ተፈሪ ለገሰ እና ደስታ ተገኝ አበጋዝ የተባሉ አደገኛ የሕገ-ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በሚዲያ አማካኝነት ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በተጨማሪም ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ እነ-ብዙአየሁ አጉቸዉ በሃይሉ፣ እራህመት አበበ እሸቴ እና እያሱ አየለ ሀብቴ የተባሉ የሀገር ውስጥ ተባባሪዎችንም በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ፖሊስ እነ-ዳውድ ተፈሪ ለገሰ፣ እራህመት አበበ እሸቴ፣ ኢክረም ሞሐመድ አያሌዉ፣ ብዙአየሁ አጉቸዉ በሃይሉ፣ እያሱ አየለ ሀብቴ እና አድማሱ ተፈሪ ለገሰ የተባሉ ዋና አደገኛ እና በሀገር ውስጥ ተባባሪ አዘዋዋሪዎች በዜጎች ላይ ፈጽመውት በነበረው ድርጊት ላይ ያካሄደውን የምርመራ መዝገብ በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች አጠናክሮ ለፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ልኳል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም ስድስቱ ተጠርጣሪዎች ለየብቻቸው በተሳተፉባቸው ሕገ-ወጥ ድርጊቶች መሠረት በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ እና ለ) እንዲሁም በሰው መነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 11(3) ሥር የተደነገጉትን በመተላለፋቸው በአጠቃላይ 31 የተለያዩ የወንጀል ክሶችን በመመሥረት ለፍርድ ቤት አቅርቧል።
ኢክረም ሞሐመድ አያሌዉ እና አድማሱ ተፈሪ ለገሰ የተባሉ ተጠርጣሪዎች በሌሉበት የምርመራ መዝገብ ተጣርቶባቸው በፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአደገኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት ተጠርጥሮ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዱባይ በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ ሀገር ተላልፎ የተሰጠው ደስታ ተገኝ አበጋዝ የተባለው ተጠርጣሪ በሌላ የወንጀል የምርመራ መዝገብ እየተጣራበት እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች ሀገራት የፖሊስ ተቋማት እና ከኢንተርፖል ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር፣ በሽብርተኝነት እና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የሚፈለጉ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ ለማቅረብ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፖሊስ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታውቋል።