የባህር በር ለኢትዮጵያ እድገትና ሉዓላዊነት ወሳኝ ነው

You are currently viewing የባህር በር ለኢትዮጵያ እድገትና ሉዓላዊነት ወሳኝ ነው

AMN- መስከረም 8/2019 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ እድገትና ሉዓላዊነት ወሳኝ መሆኑን የቀድሞ የኢትዮጰያ ባህር ሃይል አባል ሌፍትናት ኮማንደር መረባ አቶምሳ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከረጅም ጊዜ ታሪካዊ ዳራ ጋር የተያያዘ ነው።

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የባህር ኃይል ኮሌጅ ገብተው ለአምስት ዓመታት ከተማሩ በኋላ ከራስ ካሳር እስከ ራስ ዱሜራ ሌሊትና ቀን ፓትሮል በማድረግ የሀገርን ሉዓላዊነት ሲያስከብሩ የቆዩት የቀድሞ የኢትዮጰያ ባህር ሃይል አባል ሌፍትናት ኮማንደር መረባ አቶምሳ የታሪኩ ህያው ምስክር ናቸው፡፡

ሌፍትናት ኮማንደሩ እንዳስታወሱት፤ የኢትዮጵያን ብልፅግና በማይፈልጉ አካላት ፍላጎት እንዲሁም በፖለቲካና በርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ምክንያት የባህር ኃይሉ ተበትኖ እንዲቀር መደረጉ በወቅቱ የነበሩ አባላትን “የታለ ባህሩ?” ወደሚል ከባድ ቁጭት ውስጥ ከቷቸው አልፏል፡፡

ቀይ ባህርን “የዓለም ደምስር” ሲሉ የሚገልጹት ሌፍትናት ኮማንደር መረባ፤ አካባቢውን መቆጣጠር ዓለምን ከመቆጣጠር ጋር እኩል መሆኑን ጠቅሰው፤ ለኢትዮጵያ እድገትና ሉዓላዊነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ይህ የትላንት ቁጭት አሁን ላይ የመላው ኢትዮጵያውያን እና የመንግስት የገዘፈ ብሔራዊ አጀንዳ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት “የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከአምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው” በማለት የሀገሪቱን አቋም ማንፀባረቃቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ቁጭት እና ፍላጎት በተቋማዊ አሰራር፣ ቅርጽና አደረጃጀት ባለመታገዙ ምክንያት ኢትዮጵያውያን የባህር በር ፍላጎታቸውን በሚገባው ልክ ለዓለም ለማስታወቅ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡

የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ወደ አደባባይ ለማውጣት የነበረውን ይህንን እንቅፋት ለማስወገድ ምሁራን የናይል እና የቀይ ባህር ፎረምን ለመመስረት ጉዞ ጀምረዋል፡፡

የፎረሙ ሰብሳቢ አበበ ገመቹ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ጥያቄውን ዘላቂ እና ወጥነት ባለው መንገድ ይዞ ለመቀጠል ተቋም ያስፈልጋል፡፡

ሰብሳቢው አክለውም የኢትዮጵያ ጥያቄ ፍትሃዊ መሆኑን ለዓለም እና ለሀገር ውስጥ ህዝብ ማስተዋወቅ የምሁራን ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥያቄ የቀረበው በሰጥቶ መቀበል፣ በሊዝ እና አብሮ በማደግ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረጉ መንገዶች በድርድር ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት በምሁራን እይታ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት አካሂዷል።

ቀይ ባህርና አባይን ከኢትዮጵያ ነጥሎ ማየት ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን ይህንን የተሳሳተ ትርክት ለመቀየር በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በፓናል ውይይቱ የተሳተፉት ምሁራንም አባይና ቀይ ባህርን በተመለከተ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን የኢትዮጵያን እውነትና ፍላጎት ለዓለም ለማስታወቅ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን በአቋም መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review