AMN መስከረም 8/2019
የህወሃት ቡድን ከጥፋትና ከመከራ ውጪ ለትግራይ ሕዝብ ሊሰጠው የሚችለው አንዳችም አዲስ ነገር እንደሌለው የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
የትግራይ ሕዝብና ወጣቶች የሕወሃትን አጥፊ ቡድን በመታገል ክልሉን ወደ ሰላምና ልማት መመለስ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ህወሃት ባለፉት ዓመታት የትግራይን ህዝብ ማለቂያ የሌለው መከራ እና የጥፋት አዙሪት ውስጥ ከመክተት ውጪ የፈየደለት ነገር እንደሌለ ነው የተናገሩት።
የቡድኑ አጥፊ አካሄድ የትግራይ ሕዝብ ከልቡ ከሚሻው እውነተኛ የሰላም እና የመረጋጋት ፍላጎት ጋር ፍጹም የተቃረነ መሆኑን አመልክተዋል።
የሀገርና የዓለም ሁኔታ በተለወጠበት በአሁኑ ወቅት የህዋሃት መሪዎች በአሮጌ እና በጠባብ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተዘፍቀው እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ የደረሰው ጥፋት ከህወሃት ቡድን የተሳሳተ ውሳኔ የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።
አመራሮቹ ሁልጊዜ ራሳቸውን ትክክለኛ አድርጎ የማሰብ አባዜ፣ የህዝቡን እውነተኛ ስቃይ እንዳይረዱት አድርጓቸዋል ነው ያሉት።
በአሮጌ የትጥቅ ትግል ስልት የታወሩ እና ዕድሜያቸው የገፋ ጥቂት የቡድኑ አመራሮች የትግራይን ህዝብ ዕጣ ፈንታ በብቸኝነት ለመቆጣጠር መነሳታቸው ፍጹም ስህተት ነው ብለዋል።
ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ አዲስ አስተሳሰብ እና እውነተኛ የሰላም ፍላጎት እንዳለው ገልጸው ይሁንና የቡድኑ አመራሮች ጊዜው ባለፈበት እሳቤ ህዝቡን ወደ ሌላ የትርምስ አዙሪት ውስጥ ለመክተት እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተፈረመው ጦርነትን ለማስቆም እና ሕዝቡን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ እንደነበር አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ የህወሓት አመራሮች ስምምነቱን የራሳቸውን ስልጣን ለማስቀጠል ሲሉ ሂደቱን ሆን ብለው ማደናቀፋቸውን ተናግረዋል።
ከቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ጭምር ወደ ቀያቸው እንዳይመሎሱ በመከልከል ለፖለቲካ ንግድ መጠቀሚያ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
ሰላም የማይፈልጉት የህወሃት ቡድን አመራሮች ሕዝቡን በችግር ላይ ጥለው፣ ከቀውሱ ትርፍ ለማግኘት በሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድና የወርቅ ዝውውር ላይ ተሰማርተዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የትግራይ ወጣቶች በቡድኑ በሚደርስባቸው ግፍና ጭቆና ተማረው ክልሉን ጥለው እየተሰደዱ ስለመሆኑም ነው የገለጹት።
አሁን ላይ ደግሞ የቡድኑ አመራሮች የትግራይን ህዝብ ደህንነትና ጥቅም ወደ ጎን በመተው ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች ጋር አዲስ የፖለቲካ ጥምረት መፍጠራቸው እጅግ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።
የሕወሃት አመራሮች ውድቀትን እንደ ብቃትና ድል አድርገው የማየት አባዜ የተጠናወታቸው ጸረ ህዝብ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፤ ቡድኑ አጥፊ ስህተቶቹን አምኖ ከመቀበል ይልቅ ራሱን ትክክለኛ በማስመሰል ህዝቡን በማሳሳት ዘመቻ አሁንም መቀጠሉን ገልጸዋል።
የህወሓት ቡድን ለትግራይ ሕዝብ ከጥፋት፣ከስደት፣ ከስቃይ እና ከመከራ ውጪ ሊሰጠው የሚችለው አንዳችም አዲስ ነገር የለም ብለዋል።
እውነተኛ ሰላም ሊመጣ የሚችለው ይህንን አጥፊ ቡድን በቁርጠኝነት በመታገል ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የትግራይ ሕዝብና ወጣቶች የጥቂቶች መጠቀሚያ የሆነውን ይህንን አጥፊ ቡድን በመታገል ክልሉን ወደ ሰላምና ልማት መመለስ እንዳለባቸውም ማቅረባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡