የቱሪዝም ዘርፍ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶ

You are currently viewing የቱሪዝም ዘርፍ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶ

AMN – መስከረም 12/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የዘመናት ታሪካዊ ቅርሶቿን፣ እምቅ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን እና ሁለገብ የባህል እሴቶቿን ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ጋር በማስተሳሰር የቱሪዝም ዘርፉን የኢኮኖሚዋ ዋና ምሰሶ ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በተቀረጹት «ገበታ ለሀገር» እና «ገበታ ለትውልድ» ሀገራዊ ጥሪዎች አማካኝነት የተከናወኑት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ገጽታ ሙሉ በሙሉ እየቀየሩት ይገኛሉ።

ባለፉት ዓመታት በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እውን በተደረጉት እና አሁንም በግንባታ ላይ በሚገኙት ታላላቅ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች፣ ሀገሪቱ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች መዳረሻነት የነደፈቻቸውን እቅዶች በከፍተኛ ደረጃ ከፍ እያደረገችው ትገኛለች።

እነዚህ ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራትን የስበት ማዕከልነት እና ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርጉ እንደሚሆኑ ታምኖበታል።

በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞች እጅግ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሆኑ ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ ለአብነትም በአዲስ አበባ የተገነቡት የሸገር፣ የእንጦጦ እና የወዳጅነት ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየምና የዓድዋ መታሰቢያ ፕሮጀክቶች ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ብቻ ሳይሆን፣ ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እጅግ ውብ የዕረፍትና የመዝናኛ ስፍራዎች አድርገዋታል።

በክልሎችም ቢሆን በ«ገበታ ለሀገር» እና «ገበታ ለትውልድ» ማዕቀፎች በደቡብ እንደ ኮይሻ እና ሃላላ ኬላ፣ በአማራ ክልል እንደ ጎርጎራ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ደግሞ እንደ ወንጪ ያሉ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቦታዎች በዘመናዊ መሠረተ ልማቶች፣ የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝሙ ምቹ ሎጆች፣ የመዋኛ ስፍራዎች እና የብርቅዬ እንስሳት መገኛ የሆኑ ፓርኮች ትላልቅ የኢኮኖሚ ምንጮች እየሆኑ ነው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች የተፈጥሮ ጸጋዎችንና ታሪካዊ ቅርሶችን ከዘመናዊ መስተንግዶ ጋር በማጣመር ለአካባቢው ኢኮኖሚ አዲስ ሕይወት ከመዝራትም ባለፈ ወጣቱ በዘርፉ ሥልጠና ወስዶ ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲያገኝም ታቅደው የተሠሩ ናቸው።

እነዚህ በስትራቴጂካዊ ማዕቀፎች የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ተፈጥሯዊ ውበታቸውን ጠብቀው እንዲለሙ መደረጉ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ፣ የሆቴል፣ የትራንስፖርት፣ የአቪዬሽን እና የሰፊው አገልግሎት ዘርፍ እንዲያብብ አድርጓል።

ከባህል ዕደ ጥበብ እስከ አገር ውስጥ ምርቶች ግብይት እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ድረስ ያለው ሰንሰለት እንዲነቃቃ በማድረግ ረገድ እነዚህ ፕሮጀክቶች ያላቸው ሚና እጅግ የላቀ ነው።

የቱሪዝም ዲፕሎማሲን ከማጠናከር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደግ አንጻር እየተከናወኑ እና የታቀዱት እነዚህ ሥራዎች ኢትዮጵያ ከድህነት አዙሪት ወጥታ በሰፊው የብልጽግና ምዕራፍ ላይ መሆኗን በግልጽ የሚያረጋግጡ ናቸው።

የትናንቱን ተግዳሮቶች በዘመናዊ ዕውቀት፣ በስትራቴጂክ ዕቅድ እና በጠንካራ አሠራር በመቀየር የነገዋን የኢኮኖሚ ከፍታ እውን እያደረጉ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችና ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ያረጋግጣሉ።

በተለይም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑ ለስኬቱ ተጨማሪ ምዕራፍ ከፍቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ በረራዎችን በማስፋፋት እና አዲስ እየተገነባ የሚገኘውን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከመሰል የቱሪስት መዳረሻዎች ጋር በማስተሳሰር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መንገደኞችን ወደ ሀገሪቱ ለመሳብ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል።

በጥቅሉ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለው ሥር ነቀል ለውጥ ሀገሪቱ ያላትን ድብቅ አቅም በብቃት ጥቅም ላይ ማዋል መቻሏን የሚያሳይ ነው።

የትናንት ተግዳሮቶችን ተሻግረው አሁን ላይ እውን የሆኑት እነዚህ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች፣ የነገዋን ሁለንተናዊ የኢትዮጵያ ጉዞ በጸና መሠረት ላይ የሚያስቀምጡ ታሪካዊ ስኬቶች ናቸው።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review