AMN መስከረም 15 ቀን 2019 ዓ/ም
ከዛሬ ከመስከረም 15 ቀን 2019 ጀምሮ ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌት በአዲስ አበባ ማሽከርከር እንደተከለከለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ።
አንዳንድ ወንጀል ፈጻሚዎች ሞተር ብስክሌትን በመጠቀም የቅሚያ እና የስርቆት ወንጀል ሲፈጽሙ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸውም ይገኛል።
ወንጀል ፈጻሚዎች ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር እና የተሰረቁ እቃዎችን ለማጓጓዝ ሞተር ብስክሌትን በብዛት እንደሚጠቀሙ ፖሊስ አስታውቋል።
ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች የትራፊክ ደንቡን እንደማያከብሩ በተለይ ቀይ መብራትን መጣስ፣ ሌሎች ተሽከርካሪዎችን በመግጨት ማምለጥ፣ ሄልሜት ሳያደርጉ ማሽከርከር፣ የተፋፋቀ እና ለእይታ አስቸጋሪ የሆኑ የሠሌዳ ቁጥሮችን መጠቀም በአሽከርካሪዎቹ በስፋት የሚስተዋሉ የደንብ ጥሰቶች መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ወንጀልን ለመከላከል እና በሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች የሚፈጸምን የደንብ ጥሰት ለመቆጣጠር ከዛሬ ከመስከረም 15 ቀን 2019 ዓ/ም ጀምሮ ከኮድ 4 እና ከፖሊስ ሞተር ብስክሌት ውጭ በአዲስ አበባ ከተማ ባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌት ማሽከርከር መከልከሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች እና ባለ ንብረቶች አስፈላጊውን እንዲፈጽሙ ፖሊስ አሳስቦ ነገር ግን ይህንን ማሳሳቢያ በሚተላለፉ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታውቋል።