AMN መስከረም 16/2019
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለ2019 ዓ.ም የመስቀል እና የደመራ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ጉባኤው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 ቀናት የሚከበረው የደመራና የመስቀል በዓል ከታሪካዊና መንፈሳዊ ፋይዳው ባሻገር ሕዝባችን በአብሮነት፣ በፍቅርና በሰላም እንዲኖር ያስቻለ ታላቅ ሀገራዊና ሃይማኖታዊ እሴት ነው፡፡
የመስቀል በዓል ታሪካዊ መሠረት ከክርስቶስ ልደት ከሶስት መቶ ዓመታት በኋላ እንደሚጀምር የጠቀሰው መግለጫው፤ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በሰማይ የታየውን የመስቀል ምልክት ተጠቅሞ ድል ከተቀዳጀ በኋላ እናቱ ንግሥት እሌኒ እውነተኛውን መስቀል ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ፣ ደመራ ደምራና ዕጣን አጪሳ ጢሱ ባረፈበት ቦታ ቁፋሮ በማስጀመር በ326 ዓ.ም መጋቢት 10 ቀን እውነተኛውን መስቀል ማግኘቷን አብራርቷል፡፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ድል የተጎናጸፍንበት፣ ሰላም የተሰበከበትና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ወደር የሌለው ፍቅር በተግባር ያየንበት መሆኑን ነው ያመላከተው መግለጫው፡፡
መስቀል የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁበትና የኃጢአት ዕዳ የተከፈለበት የማዳን ምሥጢር እንዲሁም የአደባባይ የእርቅ ሰነድ መሆኑን አብራርቷል፡፡
በዓሉ በልብ ውስጥ ያለና በተግባር የተገለጠ ፍቅርን፣ የተቀበረ እውነትን መግለጥ እንደሚቻል ማሳያ እንዲሁም የመታመን እና የትጋት ሽልማት ምልክት መሆኑን ጉባኤው በመግለጫው ገልጿል፡፡
በተጨማሪም የመስቀልና የደመራ በዓል ኢትዮጵያውያንን በአንድነት የሚያሰባስብ ታላቅ የማኅበራዊ ትስስር መሠረት መሆኑን ጠቁሞ፤ የደመራ እሳት ጥላቻን እና መለያየትን በማቃጠል በምትኩ ይቅርታን እና ፍቅርን የምንሰብክበት፣ በልባችን ያለውን ጥል አውጥተን በመጣል እርቅን የምናውጅበት እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ጥቂት የብርሃን ጭላንጭል ጨለማን የማስወገድ ጉልበት እንዳላት ሁሉ፣ ሕዝቡ የሕይወትን ብርሃን የሚያደበዝዘውን የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የቂምና በቀል ጨለማን ለማስወገድ የሚረዳውን የመንፈስ ብርሃን ሊታጠቅ እንደሚገባ ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዓሉ የኢትዮጵያን ማኅበራዊ መስተጋብር፣ እንግዳ ተቀባይነት እና ባህላዊ እሴቶች ለዓለም የሚያስተዋውቅ ታላቅ ቅርስ በመሆኑ፤ የሃይማኖት መሪዎችና ምእመናን የጥላቻና የግጭት መንፈስ የሚወገድበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የመስቀልና የደመራ በዓልን ስናከብር አቅመ ደካሞችን፣ የተሰደዱትንና በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በመርዳትና በመተጋገዝ የእግዚአብሔርን ፍቅር በተግባር ማሳየት እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአክብሮት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡