የባንዳዎች ስር ከታሪካዊ ጠላታችን የሚመዘዝ ነው!

You are currently viewing የባንዳዎች ስር ከታሪካዊ ጠላታችን የሚመዘዝ ነው!

AMN መስከረም 16/2019

ኢትዮጵያ የብዙ ዘመናት እድሜ ባለጸጋ፣ የሉዓላዊነት እና የነጻነት ተምሳሌት የሆነች ሀገር ናት። ይሁን እንጂ የዚህች ታላቅ ሀገር ረጅም ታሪክ ከውጭ ከሚመጡ ተፅዕኖዎች እና ከውስጥ ከሚፈጠሩ መሰናክሎች ጋር የተቆራኘ ነው።

ዛሬም ቢሆን የሀገራችንን ሰላም እና ዕድገት ለማጨናገፍ የሚደረጉ ጥረቶች ከታሪካዊ ጠላቶች እና ከእነሱ ጋር ከወገኑ የውስጥ ባንዳዎች የሚመነጩ መሆናቸውን በአጽንኦት መገንዘብ ይገባል። ኢትዮጵያ እጅግ ሰፊ ለም መሬት፣ የውሃ ሃብት፣ ማዕድናት እና ብዝሃ ሕይወት ያላት ሀገር ናት። ሀገራችን በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ከሚገኙ እምቅ አቅም ያላቸው ሀገራት ግንባር ቀደም ነች። ይሁን እንጂ፣ ይህ ትልቅ የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት ባለጸጋነቷ ከሕዝቧ የኑሮ ደረጃ ጋር ያለመጣጣሙ ሀቅ ፍንትው ብሎ የሚታይ ነው።

ኢትዮጵያ በሰላም እጥረት እና በውስጣዊ አለመረጋጋት ሳቢያ አቅሟን በሚገባት ልክ መጠቀም አልቻለችም። ለኢትዮጵያ ሰላም ማጣት እና አለመረጋጋት በቋሚነት የሚሰራው ዋነኛው የውጭ አካል የግብፅ መንግስት መሆኑን ታሪካዊ እና ወቅታዊ መረጃዎች በግልጽ ያሳያሉ።

የአባይ ወንዝ ፍሰትን በተመለከተ ካይሮ የምትከተለው ፖሊሲ የኢትዮጵያን የመልማት መብት ሙሉ በሙሉ ለመገደብ ያለመና በምቀኝነት ላይ የቆመ ነው። ይህች ሀገር በታሪክም ሆነ በዘመናችን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመሸርሸር፣ የውስጥ ባንዳዎችን በመደገፍ እና የዲፕሎማሲ ጫናዎችን በመፍጠር ረገድ ግንባር ቀደም ሆና ቆይታለች።

የካይሮ መንግስት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማዳከም ያልሞከረው መንገድ አለ ማለት አይቻልም። በቀጥታ ጦር ከማዝመት ጀምሮ የውስጥ ባንዳዎችን በመደገፍ ሀገራችንን እረፍት እስከመንሳት የዘለቁ እርምጃዎችን ሲወስድ ኖሯል፡፡

በኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም እንዳይሳካ ማድረግ የግብፅ ስልታዊ ስራ ሆኖ ቀጥሏል። የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከመጀመሪያው አንስቶ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በዲፕሎማሲ መስኮች ሁሉ ለማደናቀፍ የተደረጉት ጥረቶች የዚህ እውነት ማሳያዎች ናቸው። በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዳይሰፍን እና ሉዓላዊነታችንን ተጠቅመን እንዳንለማ የሚደረገው ዘመቻ ሁሉ ከዚህ ታሪካዊ ጠላት ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም የሚመነጭ ነው።

ለዚህ ደግሞ ያለግጭት መኖር የማይችለውን የኤርትራ መንግስት በመሳሪያነት ይጠቀማል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎች የጥፋት ስራቸው ሲመዘዝ ከውጭ ጠላቶች ጋር በጥልቀት የተሳሰረ ነው። እነዚህ የውጭ ተላላኪዎች ከጠባብ የጥቅመኝነት አስተሳሰብና ተግባር ውጭ ለሀገር የሚቆረቆሩበት አንዳችም እንጥፍጣፊ ሞራል የላቸውም። ይህ የባንዳዎች መረብ ከአስመራ እስከ ካይሮ ባሉት ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የሚመራ እና የሚደገፍ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው።

ከጉያዋ ወጥተው የውጭ ኃይሎች ተላላኪ የሆኑት ባንዳዎች አቅማቸው ከመፍጨርጨር አልፎ አያቅም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ስንትና ስንት የውጭ ወረራዎችን እና የውስጥ ከዳተኞችን ድል አድርጋ ያለፈች ሀገር ናት። እነዚህ የውጭ ርዝራዦች የሚፈጥሩት ጊዜያዊ ሁከት የሕዝባችንን የጸና አንድነት ሊያናውጠው አቅም የለውም።

የኢትዮጵያ ኃይል የሚመነጨው ከሕዝቧ ጥንካሬ እና ከታሪካዊ ጽናቷ እንጂ ከከዳተኞች ሴራ አይደለም። ይህንን መሰረታዊ እና ቁልፍ ነጥብ በጥልቀት መረዳት መፍትሔው ላይ ለመድረስ እና በጋራ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለመቆም ወሳኝ ጉዳይ ነው። ግብፅ ለብሔራዊ ጥቅማችንና ሰላማችን ታሪካዊ ጠላት መሆኗን ከመሽኮርመም ወጥተን በግልጽ መገንዘብ ይገባናል።

ኢትዮጵያውያን በጋራ አቋም ብሔራዊ ጥቅማችንን ላለማስደፈር ወቅቱ የሚጠይቀውን የሀገርን ሰላምና አንድነት የማስጠበቅ የአርበኝነት ተግባራችን በተግባር ማሳየት ይገባናል!

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review