በጸረ-ኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካዊ ጫና ያልተበገረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

You are currently viewing በጸረ-ኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካዊ ጫና ያልተበገረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

AMN – መስከረም 16/2019 ዓ.ም

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍና በቀጣናዊ መድረኮች በርካታ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች አጋጥመውታል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የልማት መብት ለመገደብ የተደረጉ ሴራዎችም ብዙ ርቀት ተጉዘዋል።

ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ለመቀልበስ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች።

ግብፅ የግድቡን ጉዳይ የአረብ ብሔራዊ ደህንነት ስጋት በማስመሰል፣ የአረብ ሊግ አባላት በኢትዮጵያ ላይ ወጥ አቋም እንዲይዙና ዲፕሎማሲያዊ ማዕቀብ እንዲጥሉ ስትወተውት ከርማለች፤ ይሁን እንጂ ጥረቷ ከግብ አልደረሰም።

ግድቡ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት እንደሚጎዳ እና በቀጣናው ላይ ከባድ የውሃ እጥረት እንደሚፈጥር በማስመሰል፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ እንዲነሳሳ መጠነ ሰፊ የስም ማጥፋትና የዲፕሎማሲ ዘመቻዎች ተካሂደዋል።

ከአስመራ እስከ ካይሮ ባሉት ኃይሎች የሚመራውና የሚደገፈው ይህ የጥፋት መረብ፣ በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍንና በምጣኔ ሀብት እንዳትለማ ለማደናቀፍ ቀንና ሌሊት ሰርቷል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ ውስጥ አልፎ አልፎ የሚነሱ ውጥረቶችንና የፖለቲካ አለመግባባቶችን እንደ ልዩ ዕድል በመጠቀም፣ ለተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች ድጋፍ በማድረግ የሀገሪቱን የድርድር አቅም ለማዳከምና ሰላሟን ለማናጋት ጥረት ታደርጋለች።

ግብጽ እነዚህን ጽንፈኛ ኃይሎች በመደገፍ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ደህንነት እንዲሁም ልማት ለማደናቀፍ የሴራ ሰንሰለቶችን ብትዘረጋም፤ ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች ፈጽሞ ሊበግሩት ያልቻሉት ኢትዮጵያ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዛሬ ላይ ከቱሩፋቱ መቋደስ ችላለች።

ኢትዮጵያ እነዚህን ሁሉ የውጭና የውስጥ ጫናዎች በጽናት በመቋቋም ፍትሃዊ እና ተመጣጣኝ የውሃ አጠቃቀም የሚለውን መርህ አጽንታ ይዛለች።

የሦስቱን ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ አቀራረብ ላይ በማተኮርም የናይል ተፋሰስ ሀገራትን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አጽድቃለች።

ከዚህም በላይ በውስጣዊ ሀገራዊ አንድነትና በሕዝብ ሁለንተናዊ ድጋፍ የግድቡን ግንባታ በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ የበላይነትን አስመዝግበለች።

ዛሬ ግድቡ በኃይል ማመንጨት፣ በኢኮኖሚ እድገት እና በቀጣናዊ ትስስር ረገድ እያስገኘ ያለው ሁለገብ ጠቀሜታ የተፋሰሱን ሀገራት እውነተኛ ተጠቃሚነት አረጋግጦ ቀጥሏል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review