ሀገረ መንግሥት ማጽናትና ተቋማት ግንባታ ላይ ዘላቂ መሠረት እየተጣለ ነው

You are currently viewing ሀገረ መንግሥት ማጽናትና ተቋማት ግንባታ ላይ ዘላቂ መሠረት እየተጣለ ነው

AMN – መስከረም 15/2019 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ጠንካራና ዘላቂ የሀገረ መንግሥት ግንባታን እውን ለማድረግ እንዲሁም ገለልተኛና ብቁ ተቋማትን ለመመሥረት በሚደረገው ጥረት አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት በጸጥታ፣ በዲሞክራሲ፣ በፍትሕ፣ በአገልግሎት እና በኢኮኖሚ ዘርፎች የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ማሳየት ጀምረዋል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት ግንባታ ነው። የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የደኅንነት ተቋማት ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ እንዲወጡ ተደርገው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደራጀታቸው፣ የሀገረ መንግሥቱን ጽናት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ እንደ ማገር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ከዚህ ጎን ለጎን የዲሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት ረገድም ትልቅ እርምጃዎች ተወስደዋል። ቀደም ሲል የዲሞክራሲ ምህዳሩን ያጠበቡ እና የመልካም አስተዳደር እሴቶችን የሚፃረሩ ነባር ሕጎች እንዲከለሱ ተደርጓል።

የተደረጉት የሕግ ማሻሻያዎች የፍትሕ ሥርዓቱ በነፃነት እንዲሠራ ያስቻሉት ሲሆን፤ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ መሆኑ በአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር እውቅና ማግኘቱ ነው።

የምርጫው ታዛቢዎችም ሂደቱ ለአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ልምድ እንደተገኘበት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በፖለቲካዊና ማኅበራዊው ዘርፍ ከተከናወኑት አበይት ሥራዎች ሌላው፣ የኢትዮጵያ ያደሩ ችግሮች ለመቅረፍ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካኝነት በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት መደረሱ ሲሆን ይህም አዲስ ማኅበራዊ ውል ለመመሥረት ትልቅ መሠረት ጥሏል።

በሌላ በኩል በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ ሰፊ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን፤ የዲጂታል መታወቂያ፣ የኤሌክትሮኒክስ ፋይናንስ እና የዘመናዊ የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቶችን ማዘመን መቻሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን ከመጨመሩም በላይ ለሙስና አሠራር ተጋላጭነትን በእጅጉ ቀንሷል።

በአጠቃላይ በሀገረ መንግሥት ግንባታና ተቋማት ማጠናከር ሂደት በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ግቡን እንዲመታ የተጀመሩ የማሻሻያ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review