AMN – መስከረም 15/2019 ዓ.ም
ባለፉት 5 ዓመታት በሀገሪቱ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በተቋማት ግንባታ ዘርፎች በርካታ ለውጦች መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ሂደቱ ከመዋቅር አልፎ ወደ እውነተኛ አቅም ግንባታ የተሸጋገረበት እንደነበር አብራርተዋል።
በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚያዊ አሠራሮች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት ሙሉጌታ(ዶ/ር)፣ መንግሥታዊ ተቋማት ከመዋቅር ባለፈ ሀገርን አፅንተው የሚያሻግሩ አቅሞች መፍጠራቸውን አንስተዋል።
በተለይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን፣ የፌዴራል ፖሊስን እና የቴክኖሎጂ ተቋማትን አቅም በዘመናዊ መንገድ በመገንባት ረገድ ትልቅ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መንግሥት የሚዋቀረው በሕዝብ ውሳኔና በምርጫ ሂደት ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ የገለጹት ተመራማሪው፣ አዲስ የሚቋቋም መንግሥት ከሕዝብ ጋር የሚገባው ውል የሀገርን ሉዓላዊነትና ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥ መሆን እንዳለበት አሳሰበዋል።
የሀገሪቱ የመንግሥት ሥርዓት በምርጫ ውጤት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ አሸናፊው ፓርቲ ከሕዝብ ጋር ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የፖለቲካ ውል ይፈራረማል።

ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ጊዜ ሐሳባቸውንና ፖሊሲዎቻቸውን ለሕዝብ አቅርበው ሕዝቡ የሚሻለውን አካል በዕውቀት መርጦ ውሳኔ እንደሚሰጥበት የጠቆሙት ሙሉጌታ (ዶ/ር)፣ በቅርቡ የሚመሰረተው አዲሱ መንግሥትም ከዚህ ቀደም የነበሩ አፈጻጸሞችን በመገምገም ሀገርን በጽናት የማቆም ኃላፊነት እንዳለበት አንስተዋል።
የሀገርን ጽናትና ዘላቂ ዕድገት እውን ለማድረግ ሥራና አሠራርን በመዘርጋት ካቢኔዎችንና ተቋማትን ማዋቀር፣ የተገባውን ቃል እና የኢኮኖሚና የብሔራዊ ጥቅም ፖሊሲዎችን መፈተሽ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍና የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ለውጦች ከሀገር ውስጥ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማቀናጀት ሁለትዮሽና ብዙዮሽ ግንኙነቶችን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ ተመራማሪው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያላቸው እና በራሳቸው የጸኑ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያሉት መሆኑ የሀገሪቱን ፌዴራላዊ ሥርዓት ጠንካራና የማይነቃነቅ አድርጎታል።
በመሆኑም አዲሱ መንግሥት በጠንካራ ተቋማዊ አሠራርና በሕዝብ ትብብር ሀገሪቱን ወደ ከፍታ ማሸጋገር እንደሚጠበቅበት ተመላክቷል።
የኢኮኖሚውን ዘርፍ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣ ሀገሪቱ በችግሮች ውስጥ አልፋ ጠንካራ የመቋቋም አቅም ማሳየቷን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሮች የተከናወኑት ትላልቅ መዋቅራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አመልክተዋል።
በመጨረሻም በሀገሪቱ የነበረው የዜሮ ድምር የፖለቲካ አካሄድ ቀርቶ፣ በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ የተመሠረተ የጋራ ሐሳብ እና የትብብር መንፈስ ፖለቲካዊ አቀራረብ እየሰፈነ መምጣቱ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ጎዳና እያሸጋገራት ይገኛል ብለዋል።
በወርቅነህ አቢዮ