የአብሮነት እሴቶች የአዲስ አበባ ድምቀት!

You are currently viewing የአብሮነት እሴቶች የአዲስ አበባ ድምቀት!

AMN – መስከረም 15/ 2019 ዓ.ም

የመስቀል ደመራ እና ኢሬቻን የመሳሰሉ በዓላት ሚሊዮኖች በአብሮነት የሚደምቁባቸው ፣ ማህበራዊ መስተጋብር ከፍ ብሎ ለዓለም የሚታይባቸው ፀጋዎች በመሆናቸው የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ከፍ ያደርጋሉ፡፡

የአደባባይ በዓላት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ፣ ጥልቅ ባህሎች እና ዘርፈ-ብዙ ማኅበራዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ የጋራ ሀብቶች ናቸው፡፡

በዓላቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይዳሰሱ ቅርሶች በመሆናቸው ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ካበረከተቻቸው ድንቅ ስጦታዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህም የአዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻነት ያሰፉ ሲሆን፣ የሀገሪቱን የስዕበት ማዕከልነትም ከፍ አድርገዋል፡፡

የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በተለያዩ ብሔረሰቦች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ለዘመናት የቆዩትን የመቻቻል፣ የመከባበርና የሰላም እሴቶች በተግባር የሚያጸኑ ህያው መድረኮች ሆነው ዘልቀዋል።

ዜጎች የአደባባይ በዓላቱን በጋራ ደምቀው፣ በአብሮነት ተጋምደው ሲያከብሩ፣ የአግላይነት ኋላቀር እሳቤ ይወገዳል፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ይጎለብታል፡፡

የአደባባይ በዓላቶቻችን በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት መንፈስ የሚከበሩ የደስታ ቀናት ብቻ ሳይሆኑ፣በየጊዜው ሲላላ የቆየውን የኢትዮጵያውያንን ማህበራዊ ትስስር በመጠገን አብሮነትን የሚያጠናክሩ፣ የጋራ ተስፋን የሚያፀኑ የወል ማንነቶች ናቸው።

የሀገር ፍቅር ስሜትንና፣ የህዝብ ትስስርን ከማሳደግ ባሻገር እነዚህ ታላላቅ የአደባባይ በዓላት የመዲናዋን ብሎም የኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰት በመጨመር ለለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችና የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በዓላቱን በአካል ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ ስለሚገቡ፣ ከሚያመጡት የውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ የኢትዮጵያን እና የህዝቦቿን ገናና ታሪክ አውቀው የሚያሳውቁበት ምቹ ሁኔታም ይፈጠራል፡፡

በዓላትን ምክንያት በማድረግ የሚጨምረው የቱሪዝም ፍሰት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን የመጎብኘት ተነሳሽነትን ከፍ ስለሚያደርግ፣ ሆቴል እና ትራንስፖርትን ለመሳሰሉ የአገልግሎት ዘርፎች እንዲሁም በባህል አልባሳት፣ የእጅ ጥበብ ውጤቶች እና በመሰል የንግድ ተግባራት ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

የሀገርን ታሪካዊ እሴቶች ሳይበረዙ ለቀጣዩ ትውልድ በማሸጋገር፣ አዲሱ ትውልድ ቱባ ባህሉን እንዲያውቅ እና እንዲንከባከብ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩት የአደባባይ በዓላቶች የወል ትርክት ማዕከል፣ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብር ድምቀት፣ የዘላቂ ሰላም ፅኑ መሠረት መሆናቸውን በመረዳት እሴቶቻቸውን መጠበቅ ይገባል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review