ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያዊነት ላይ የጋራ ስሜት ለመፍጠር የሚያስችል ነው – ፕ/ር መስፍን ዓርዓያ

AMN – መስከረም 24/2019 ዓ.ም

ሀገራዊ ምክክር በልዩነቶች ውስጥ መግባባት ላይ ለመድረስ እና በኢትዮጵያዊነት ላይ የጋራ ስሜት ለመፍጠር የሚያስችል ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን ዓርዓያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች የተሰበሰቡትን የአጀንዳ ምክረ-ሀሳቦች በአግባቡ በማደራጀትና በኮሚሽኑ ምክር ቤት በማጽደቅ ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረክቧል።

በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን ዓርዓያ፤ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿንና ልዩነቶቿን በውይይት የመፍታት መሻቷ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክክሩም ኢትዮጵያዊያን በልዩነት ውስጥ ሆነው ተነጋግረው ለችግሮቻቸው መፍትሔ ማበጀት እንደሚችሉ ለአለም ያሳዩበት ታሪካዊ ሂደት መሆኑን አንስተዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ አራት ሺህ ተሳታፊዎች ተገናኝተው መነጋገራቸውን ጠቅሰው፤ እስከዛሬ ተገናኝተው የማያውቁ ሕዝቦች ለአንድነትና ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ስሜት አንድ ቢሆንም አተረጓጎማቸውና አካሄዳቸው የተለያየ እንደነበር አብራርተዋል።

ይህ ሂደት በልዩነቶች ውስጥ ሆነው መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻል ያሳዩበት ታሪካዊ ሂደት መሆኑንም ገልጸዋል።

አራት ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ተከባብረው፣ ተነጋግረው፣ ተደማምጠው በአራት መቶ ጉዳዮች ላይ መግባባት መቻላቸው የዲሞክራሲ መሠረት እንደሆነ በምክክሩ ታምኖበታል።

ይህ ሂደት ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን እና ለመላው ዓለም የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መንገድ መፍታት እንደሚችሉ ያስመሰከሩበት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኮሚሽኑ ምክረ-ሀሳቦቹን አቅርቦ ማጠናቀቁን ጠቅሰው፤ በቀጣይ እነዚህ ምክረ-ሀሳቦች ወደ ተግባር እንዲገቡ ሰፊ ክትትል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በተለይ አዲስ የሚቋቋመው መንግስትና ሰባተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን በጥልቀት በመገምገም፣ ክትትል በማድረግ እና ምክረ-ሀሳቦቹን ሥራ ላይ በማዋል ወደ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review