በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ መጪውን ዘመን ቀድመው አስበው ከወዲሁ በተጠንቀቅ ለሚጠብቁ ብርቱዎች ምንዳው ብዙ ሲሆን ለሚዘናጉት ደግሞ ዕዳዉ እልፍ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN- መስከረም 26/2019 ዓ.ም

መጪዉን ዘመን ቀድመው አስበው ከወዲሁ በተጠንቀቅ ለሚጠብቁ ብርቱዎች ምንዳው ብዙ ሲሆን ለሚዘናጉት ደግሞ ዕዳው እልፍ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢፌዴሪ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤ መጪው ክረምት የሚጠቅመው ላረሰዉ ገበሬ ነው እንደሚባለው ያለፈው ክፉ ቀን ተመልሶ እንዳይመጣ ለሃገሪቱ የሚበጀውን መምረጥና መከተል የዚህ ትዉልድ አደራ ነዉ ብለዋል፡፡

ዓለም የኢንዱስትሪ አብዮት ሲያካሄድ በዘመነ መሳፍንት ሽኩቻ እና በእርስ በርስ ግጭት ብዙ ነገር አጥተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ከጦርነት አዙሪት ሳንወጣ ሌላው ዓለም ሁለተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት አስተናገደ ነው ያሉት፡፡

የአውሮፓ ኃይል ቅኝ ሊገዛን አቅሙን እና ጉልበቱን አደርጅቶ ሲመጣ እኛ ግማሽ ጉልበታችን በገዛ እጃችን ተይዞ ነበር ፤ በጊዜ ተዘጋጅተን ቢሆን ኖሮ አቅማችንን ሳንጨርስ በቀላሉ መመከት እንችል ነበር ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጥያቄው ዛሬስ የት ላይ ነን የሚለው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ እንቅፋት አንዴ መመታት ተፈጥሮአዊ ቢሆንም ደጋግሞ መመታት ግን የጤና አይደለም፡፡

እንደ ሃገር ቀድሞ አለመዘጋጀት የሚያስከፍለውን ዋጋ የጣሊያንን ወረራ በማሳያነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወራሪ ሃይሉ በአድዋ ጦርነት ከተሸነፈ በኋላ ሀገሪቱን መልሶ ለመውረር ሲዘጋጅ እኛ ግን አሸልበን ነበር ነው ያሉት፡፡

ባልተዘጋጁበት ግንባር እንደመግጠም ያለ ክፉ ቀን የለም ፤ ያ የከፋዉ ቀን ተመልሶ እንዳይመጣ ካለፉት ስህተቶቻችን ተምረን ፤ አንዳችን የሌላውን እንከን መንቀስ ትተን መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

አድዋ ላይ በምድር ያገኘነው ባላንጣ በማይጨው ጦርነት በሰማይ ተመልሶ እንደመጣው ሁሉ፤ ነገ ጠላት በየት በኩል ሊጎበኘን እንደሚችል ስለማናዉቅ አስቀድመን ማሰብና መዘጋጀት ይኖርብናል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review