AMN- ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

የትውልድ ድምጽ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሀገርን ሰላም፣ ልማት እና ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የተቋሙ ምክትል ሥራ አስፈፃሚና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ካሳ ተናገሩ፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አመራሮችና ሠራተኞች “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሀሳብ 19ኛውን ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀንን በድምቀት አክብረዋል፡፡
በበዓሉ አከባበር ላይ የተቋሙ ምክትል ሥራ አስፈፃሚና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ካሳ መልእክት አስተላልፈዋል።

አቶ ጥላሁን በመልዕክታቸውም፤ የሠንደቅ ዓላማ ከፍታና ክብር የሚለካው ህዝብ በነፃነት፣ በእኩልነት እና በሰላም መኖር ሲችል እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ይህንንም ለማረጋገጥ መገናኛ ብዙሃን ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ያነሱት አቶ ጥላሁን፤ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም የሀገርን ሰላም፣ ልማት እና ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የህዝብን ሰላም እና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንደወትሮው ሁሉ ከፍ ብሎ እንዲታይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርገው ተጋድሎና መስዋዕትነት ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል።

በታምራት ቢሻው