AMN – ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

ህዝብን ያሳተፈ እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል የተናበበ የአሰራር ስርዓት አዲስ አበባ ከተማ አስተማማኝ የሰላም ባለቤት እንድትሆን ማስቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ተናገሩ።

ቢሮው የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በመገምገም ላይ ይገኛል።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ እንደገለጹት፤ በወርሃ መስከረም በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ የአደባባይ በዓላት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በድምቀት ተከብረዋል።
እነዚህ በዓላት በሰላም እና በድምቀት ይከበሩ ዘንድ የህዝቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲሁም የጸጥታ አካላት የተቀናጀ አሰራር ከፍተኛውን ድርሻ መውሰዱን ገልጸዋል።
አክለውም ቢሮው ባለፈው ሩብ ዓመት ወንጀልን ቀድሞ በመተንተን፣ በመግታት እና ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በመቆጣጠር ረገድ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል። ይህም አዲስ አበባ ከተማ አስተማማኝ የሰላም ባለቤት እንድትሆን ማስቻሉን አብራርተዋል።
አዲስ አበባ አሁን ላይ የዘመናዊነት እና የዘመናዊ አሰራሮች የልህቀት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን የጠቆሙት ወይዘሮ ሊዲያ፤ በቀጣይም የጸጥታ ኃይሉ በቴክኖሎጂ የሚመራ እና ቴክኖሎጂን የሚዘውር ይሆን ዘንድ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በተመስገን ይመር