መከላከያ ሠራዊት አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ህዝባዊነቱን ማረጋገጡን ቀጥሏል

AMN – ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ሰላምና ደህንነት ፣ የሀገር ሉዓለዊነት እንዲከበር በዱር በገደሉ መስዋዕት እየከፈለ የሚገን ህዝባዊ ሠራዊት ነው።

ሠራዊቱ በጦር አውድማ ከሚያደርገው ተጋድሎ ባሻገር በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሠማራትና አቅመ ድካሞችን በመደገፍ ህዝባዊነቱን እያስመሰከረ ይገኛል።

የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሕዝብ ደህንነትና የሀገር ታማኝነት ግዳጁን በሚወጣበት ቀጣና፣ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሰብላቸው እንዳይበላሽ ሥጋት ላይ ለነበሩ አርሶ አደሮች አራት ሄክታር የሚገመት የጤፍ ማሳ አጭዶ አስረክቧል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ ከተገነባባቸው መሠረታዊ ዕሴቶች አንዱ ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር የሚለው መመሪያ ነው። ሠራዊቱ በከባድ የግዳጅና የውጊያ ቀጠናዎች ውስጥ በሚገኝበት ወቅት እንኳን፣ በሚያገኛቸው አጫጭር ፋታ የሕዝቡን እንግልትና ችግር ለመካፈል ወደኋላ አይልም።

በሰሜን ምዕራብ ዕዝ የበላይ ዘለቀ ክፍለጦር ሬጅመንት አባላት ትጥቃቸው ሳይላላና ዝግጁነታቸው ሳይቀንስ፣ የአርሶ አደሩ የጤፍ ሰብል በዝናብ እንዳይበላሽ ሌሊትና ቀን ደክመው ማሳውን አጭደው ማስረከባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡።

የመከላከያ ሠራዊቱ መሬት ላይ እያሳየ ባለው በተግባር የተደገፈ ፍቅርና ድጋፍ ሕዝባዊ ተቀባይነቱ እያደገ መጥቷል።

ሠራዊቱ በጽንፈኛ ኃይሎች በደል ቢደርስበት እንኳ ሕዝቡን የሚያገለግል፣ የማያኮርፍና የማያቄም የሕዝብ ልጅ መሆኑን አስመስክሯል።

በጽንፈኞች የተዛባ ስም ማጥፋት ቀደም ሲል መጣብን ብለው ይሰጉ የነበሩ የአካባቢው እናቶች፣ የሠራዊቱን ቅንነትና አጋርነት ሲመለከቱ መጣልን በማለት ደረታቸውን እየደቁ ስሜታቸውን፣ ፍቅራቸውንና ናፍቆታቸውን ገልጸዋል።

ይህ በሰሜን ምዕራብ ዕዝ የታየው አርአያነት ያለው ተግባር፣ የመከላከያ ሠራዊታችን ሕዝባዊነት በጠንካራ አለት ላይ የተገነባ ዘመን የማይሽረው ዕሴት መሆኑን አረጋግጧል።

ሠራዊቱና አስተማማኙ የደጀን ሕዝብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው፣ ይህንን የተከበረ ወርቃማ ግንኙነት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review