AMN- ሰኔ 13/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማ አስተዳደሩ ቁልፍ ተግባር ተቋም መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በተቋማት እየተከናወኑ ካሉ የሪፎርም ስራዎች አንዱ በሆነው የደንብ ማስከበር ባለስልጣን፣ በ10 ዙር ሲሰለጥኑ የነበሩ ኦፊሰሮችን ማስመረቃቸውን ገልጸዋል።
የአቅም ግንባታ ስልጠናው ኦፊሰሮቹ ከህዝብ ጋር አክብሮት የተሞላበት ተግባቦት እንዲኖራቸው፣ ህግና ስርዓትን ያለአንዳች አድልዎ እንዲያስከብሩ፣ ፍፁም አገልጋይነት እንዲላበሱ እንዲሁም ስነምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የደንብ ማስከበር አፊሰሮቻችን ስታገለግሉ ህዝባችሁን በፍቅር፣ በትህትና እና በማክበር እንዲሁም የወጡ ደንቦችን የለምንም ርህራሄና ያለአድልዎ በማስከበረ እንዲሆን ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
ተቋሞቻችን በስርዓት የተገነቡ፣ ጠንካራ የአገልግሎት ስርዓት ያላቸው፣ ስነምግባር የተላበሱ፣ አገልጋይ እንዲሁም ለህዝብ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎችን እና አመራሮችን የመፍጠር ተቋማዊ የሪፎርም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ከተማዋ የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ፣ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ወታደራዊ አለባበስ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የጠበቀ እንዲሆን፣ ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት ከነበረው የደንብ ልብስ ተጨማሪ ሆኖ የሚያገለግል አዲስ የደንብ ልብስ ይፋ መደረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።