AMN- ጥቅምት 21/2019 ዓ.ም
አዲስ አበባ ልማቷን ከነዋሪዎቿ ተጠቃሚነት ጋር በማቀናጀት ይህንን እውነታ በተግባር እያሳየች ትገኛለች።
ይህም ጥረት ሌላ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አስገኝቷል። በተባበሩት መንግሥታት የሰው ሰፈራ ፕሮግራም (UN-Habitat) እና በቻይና ትብብር በተዘጋጀው የ2026 የዓለም ከተሞች ቀን ላይ የሸንሃይ ሽልማት ከተቀበሉ ከተሞች መካከል አዲስ አበባ ተካትታለች።
ይህ ዕውቅና ከተማዋ በሰው ተኮርና ዘላቂ ልማት የጀመረችውን ጉዞ በተጨባጭ ውጤቶች እያስመሰከረች መሆኗን የሚያሳይ ነው።
የሸንሃይ ሽልማት ዘላቂነትን፣ አካታችነትን፣ ሰው ተኮርነትንና የከተሞችን የተለያዩ ተግዳሮቶች የመቋቋም አቅም በማጎልበት ረገድ ስኬታማ ሥራ ለሚያከናውኑ ከተሞች የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ነው።
ስለሆነም የአዲስ አበባ ተሸላሚነት የከተማዋን ውበትና የተሻሻለ ገጽታ ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የልማት ሥራዎቿ በነዋሪዎች ሕይወት፣ በአካባቢ ጥበቃና በከተማዋ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ላይ ያሳደሩትን አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያመለክት ነው።
ይህ የከተማችን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አይደለም። በ2024 በUN-Habitat እና በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል ከተማ በተዘጋጀው የሴኡል ከተማ ሽልማት ማግኘቷ ይታወሳል። አሁን የሸንሃይ ሽልማትን ማግኘቷ ደግሞ ይህ ስኬት የአንድ ጊዜ ውጤት ሳይሆን፣ በቀጣይነት በሚመዘገቡ የልማት ውጤቶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያሳያል።
ለዚህ ዓለም አቀፍ ዕውቅና መሠረት ከሆኑት ዋና ዋና የልማት አቅጣጫዎች መካከል፦
– ሰው ተኮር የከተማ ልማት፦ የነዋሪዎችን ፍላጎት፣ ደህንነትና የኑሮ ጥራት ማዕከል ያደረገ የከተማ መልሶ ማልማት።
– የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፦ ለነዋሪዎች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ጥራቱ የተረጋገጠና ምቹ የመኖሪያ አማራጭ ለመፍጠር የተከናወኑ ሥራዎች።
– የከተማ ኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት፦ የተፈጥሮ ሀብቶችን ከከተማ ልማት ጋር በማቀናጀት ለመዝናኛ፣ ለማኅበራዊ ትስስር፣ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ለአካታች ልማት የሚያገለግሉ አካባቢዎችን መፍጠር።
– ዘመናዊና ተደራሽ ትራንስፖርት፦ የነዋሪዎችን የመንቀሳቀስ አቅም በማሳደግ የተሻሉና ተደራሽ የትራንስፖርት አማራጮችን ማስፋፋት።
– አረንጓዴነትና የአካባቢ ጥበቃ፦ ከተማዋን ንጹሕ፣ ውብ፣ አረንጓዴና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ የአካባቢ ልማት ሥራዎች።
እነዚህ የልማት አቅጣጫዎች በጋራ የሚያመለክቱት አንድ ዋና መርህ አለ፤ የከተማ ልማት ዋነኛ ዓላማ የሰውን ሕይወት ማሻሻል ነው። መሠረተ ልማት ሲስፋፋ፣ አገልግሎቶች ለሁሉም ተደራሽ ሲሆኑ፣ የኑሮ ምቹነት ሲረጋገጥና የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ሲጎለብት የልማት ትርጉም እውን ይሆናል።
በተለይም በታዳጊ አገራት ከባድ ፈተና የሆነውን የከተማ መልሶ ማልማት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ሳይጎዳ ማከናወን እንደሚቻል አዲስ አበባ በተግባር እያሳየች መሆኑን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላታል፡፡ ይህም ለሌሎች ከተሞች የሚጠቀስ ተሞክሮና ከተማን በማልማት ሂደት የሰው ልጅ ክብርና ተጠቃሚነት ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ትምህርት ነው።
ይህ ስኬት የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ዘርፍ ውጤት ብቻ አይደለም። የከተማዋን ለውጥ ለማምጣት በጋራ የተጋገዙ የአመራር፣ የባለሙያዎች፣ የሠራተኞችና የነዋሪዎች የጋራ ጥረት ውጤት ነው። ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ፣ በትጋት ለሠሩና ድጋፋቸውን ላበረከቱ ሁሉ ከልብ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
አዲስ አበባ ዛሬ የከተማዋን ገጽታ ብቻ አትቀይርም፤ ልማት በሰው ሕይወት ላይ ምን ያህል ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚችልም በተግባር እያሳየች ነው። የሸንሃይ ሽልማትም የዚህ ራዕይና የጋራ ጥረት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ነው።
ይህ ለከተማችን ኩራት፣ ለኢትዮጵያችን ክብር ከመሆኑም ባሻገር፣ የተጀመረውን የልማት ጉዞ በበለጠ ቁርጠኝነት እንድናስቀጥል የሚያነሳሳን ትልቅ ስንቅ ነው!