AMN- ኅዳር 16/2019 ዓ.ም
በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው አምስተኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ጉባኤ በሁለተኛ ቀን ውሎው ትኩረቱን በኢንቨስትመንት፣ በሀገር ውስጥ ምርት እና በጤና ሥርዓት ዘላቂነት ላይ አድርጓል።
ጉባኤው ክትባቶችን፣ መድኃኒቶችንና የሕክምና መገልገያዎችን በአህጉሪቱ ውስጥ ለማምረት የተያዘውን ራዕይ ከቃል ወደ ተግባራዊ ገበያና ምርት ለማሸጋገር የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በጥልቀት እየመከረ ይገኛል።
የአፍሪካ የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ማዕከል ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር መሰረት ዘላለም እንደገለጹት፣ ውይይቱ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለምታካሂዳቸው የነገ ጉዞዎች መጻኢ ዕድል ይፈጥራል።
ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ ድጋፍና ፋይናንስ አካላት እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች በመገኘት የባህልና የልምድ ልውውጥ እያደረጉ እንዳሉ በመግለጽ፣ ይህም በአህጉሪቱ ያለውን የጤና ሥርዓት ለማጠናከር ትልቅ መድረክ እንደሚሆን አንስተዋል።
የሀገር ውስጥ ተሳታፊዎች ጉባኤውን ማስተናገድ የጤና ፖሊሲዎችን ለማስተዋወቅ፣ አዳዲስ አጋሮችን ለመፍጠር፣ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን እንዲሁም የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማነቃቃት የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
የጉባኤው ተሳታፊ እንግዶችም ከጉባኤው ባሻገር አዲስ አበባን ስለተመለከቱበት ሁኔታ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በጉባኤው ላይ የተሳተፉ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ከካዛብላንካ ኑራግ፣ ከማዳጋስካር ኤሚሊ አደምስ እና ከቡርኪናፋሶ የመጡት ቲምኖማን ሲለሜያሜጎ፣ በአዲስ አበባ እየታየ ያለውን ሁለንተናዊ እድገትና የሕዝቡን እንግዳ ተቀባይነት በልዩ ስሜት ገልጸውታል።
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት እንግዶቹ በአዲስ አበባ ከተማ ውበት በጣም መደነቃቸውንና ከጠበቁት በላይ እጅግ የለማችና ያማረች ሆና እንዳገኟት ተናግረዋል።
ተሳታፊዎቹ ጉባኤው ስለ ወረርሽኝ ዝግጁነት፣ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ፣ ሁሉን አቀፍ ጤና እና የጤና ፋይናንስ የሚመክር በመሆኑ፣ ከሌሎች ሀገራት ልምድ ቀስሞ በየሀገራቸው ያለውን የሕብረተሰብ ጤና አገልግሎት ለማሻሻል ታላቅ የመማማሪያና የግንኙነት መድረክ እንደሆነም ገልጸዋል።

የአፍሪካን የጤና ሥርዓት ወደ ራስን መቻልና ዘላቂነት ለማሸጋገር የሚያስችለው ይህ አህጉራዊ ጉባኤ እስከ መጪው አርብ ድረስ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።
በታምራት ቢሻው