የኢንዱስትሪ አብዮት ስኬት የመንግሥትን ንቁ ተሳትፎና ስልታዊ ጣልቃ ገብነትን ይጠይቃል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኢንዱስትሪ አብዮት ስኬት የመንግሥትን ንቁ ተሳትፎና ስልታዊ ጣልቃ ገብነትን ይጠይቃል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

​AMN – ሚያዝያ 07/2018 ዓ.ም

​ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን የመንግሥት ሚና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታዩ ባሉ አዳዲስ የኢኮኖሚ ለውጦች ዙሪያ ለኢቢሲ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ የኢንዱስትሪ አብዮት ስኬት የመንግሥትን ንቁ ተሳትፎና ስልታዊ ጣልቃ ገብነትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

መንግሥት ከኢንዱስትሪ እና ከንግድ ሥራዎች መውጣት አለበት የሚለው የቀድሞው የሊበራል አስተሳሰብ በአሁኑ ወቅት እየተቀየረ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ ዘመን ኢንዱስትሪን ውጤታማ ለማድረግ የመንግሥት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት፣ የፖሊሲ እና የፋይናንስ ኢንቨስትመንት አስፈላጊ መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት እየታመነበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

​መንግሥታት ለብሔራዊ ዕድገት ሲሉ ስልታዊ በሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ያላቸውን ቁጥጥር እያጠናከሩ መሆናቸውን ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም የሀገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት የታሪፍ ተመኖችን እንደ ውጤታማ ስልት መጠቀማቸውን አብራርተዋል።

ከዚህም ባለፈ እንደ ቺፕስ (Chips) ያሉ ለቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ወሳኝ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን እና ግብዓቶችን የመቆጣጠር አቅም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በውድድር ብልጫ ለማግኘት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

መንግሥታት ብሔራዊ ደኅንነትንና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ሲሉ የመረጃ ሀብትን የመቆጣጠርና የመጠበቅ ሥራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ታዋቂ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ምርትን በቀጥታ ከመሸጥ ይልቅ፤ ወደ አገልግሎት ዘርፍ እያሸጋገሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብነት አንስተዋል።

ኢትዮጵያም እነዚህን ወቅታዊ የገበያ ለውጦች ተረድታ መተግበር እንዳለባት አስገንዝበዋል።

የኢንዱስትሪ ዕድገት ከንግድ፣ ከሎጂስቲክስ እና ከመንግሥት መመሪያዎች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ ዘርፉን ስኬታማ ለማድረግ የተቀናጀ አመራር እና የመንግሥት ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

​በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review