AMN – ሚያዝያ 09/2018 ዓ/ም
ዛሬ በዓይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ከፍተናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው መልእክት አስተላልፈዋል ፡፡
መሠረተ ልማት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ግብአቶችን በማመላለስ የኢኮኖሚያችን የደም ሥር፣ የብልጽግናችን መሠረት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዐውደ ርዕዩ የተመለከትነውም ወሳኝ የልማት ተቋሞቻችን፣ መሠረተ ልማትን እንደ ሀገር በቅንጅትና በትብብር የመምራት አዲስ የሥራ ባህል እየገነቡ መሆናቸውን ነው ብለዋል ፡፡
ባለፉት ዓመታት ፈጠራን፣ ፍጥነትን እና ጥራትን የጉዟችን መርሕ አድርገን በመሥራት ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግበናል፡፡ የመንገድ ርዝመታችንን በብዙ ኪሎ ሜትሮች አሳድገናል፤ ታዳሽ ኃይል የማመንጨት ዐቅማችንን ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት አካባቢ አድርሰናል። በዲጂታል ዘርፍም የሞባይል ተጠቃሚዎችን 97 ሚልዮን እና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር 57 ሚልዮን መድረሱን ጠቁመዋል ፡፡

በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራዎቻችን “ከተባበርን የማይቻል የለም” የሚለውን መርሐችንን በተግባር ያሳዩ፣ ፍጥነትና ጥራትን ያስተሣሠሩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውነ ጠቅሰዋል ፡፡
ጉዟችንን ለማጣጣል ለሚሞክሩም ሆነ የውጤቱ ባለቤት እኛ ነን” ለሚሉ ሁሉ መልሳችን አንድ ነው፤ እውነታውንና ፍርዱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትተን፣ ሥራችንን እንቀጥላለን! ኢትዮጵያን ለማበልጸግና ለመገንባት በየበረሃውና በየተራራው እየፈሰሰ ላለው ላብና ደም ተገቢውን ክብር እንሰጣለን ፡፡
መንግሥት በመንገድ፣ በኃይል፣ በመስኖ፣ በባቡርና በዲጂታል መሠረተ ልማት ዘርፍ ፈጣንና ፍትሐዊ ልማት ለማረጋገጥ የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

አሁን ያለንበት ወቅት የሥራ፣ የውጤት እና የተስፋ ዘመን ነው ያሉት አቶ ተመስገን ትናንት የተገነባው ለዛሬ፣ ዛሬ የምንገነባው ደግሞ ለነገው ትውልድ ኩራት እና የብልጽግና ዋስትና ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባስተላለፉት መልእክት አስፍረዋል ፡፡