AMN – ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ጠዋት የስራ ዘመኑን ሶስተኛ የ100 ቀናት የመንግሥት ሥራ አፈፃፀም ከዘጠኝ ወራት አጠቃላይ አፈፃፀም ጎን ለጎን መገምገም መጀመሩን ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእድገት አመቺ ካልነበረው እና በደካማ የተቋማት እና የፖለቲካ ማዕቀፍ፣ በታጠረ የግል ዘርፍ ተሳትፎ እንዲሁም ውጤታማ ባልነበረ የቁጥጥር ከባቢ ከሚገለጠው የኢኮኖሚ መልክ ወጥተናል ብለዋል።
የግሉ ዘርፍ ደካማ ውድድር ውስጥ ነበር፤ በመንግሥት ሥር የነበሩ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የንግድ ተቋማትም ከፍ ባለ የዕዳ ሸክም ተዘፍቀው ከአቅም በታች ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ይታወቃል ብለዋል።

ምርታማነት አሽቆልቁሎ ኢኮኖሚውም ለአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ምላሽ በሚሰጥ አዲስ ገቢር ነበብ የፓለቲካ ኢኮኖሚ መንገድ ቀይሰናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የቀየስነው አዲሱ የኢኮኖሚ አካሄድ በአጭር ጊዜ ትግበራ ጠንካራ ባለሁለት አሃዝ የእድገት ሂደትን አስመዝግቧል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚያችን በ9.2 በመቶ እያደገ ይገኛል። ይኽ እድገት በመጪው ዓመት ወደ10.2 በመቶ እንደሚያድግ እንጠብቃለን። በየዘርፉም የታቀዱ ግቦቻችንን ለማሳካት ከፍ ባለ ትጋት ቀጥለን፤ በግብርና 7.9 በመቶ፣ በኢንደስትሪ 13.2 በመቶ፣ በአገልግሎት 9.3 በመቶ ዕድገቶች ሳይቆራረጡ የሚከናወኑ ይሆናል ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
እነዚህ ጥረቶች የበለጠ ጽኑ፣ ተወዳዳሪ እና አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለንን አቋም እና የመተግበር ዐቅም ያሳያሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።