AMN-ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የተገነቡት መንገዶች ተሽከርካሪን እና እግረኛን ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው ከአሁን ቀደም ሲያጋጥሙ የነበሩ የትራፊክ አደጋ ክስተቶችን መቀነስ እንደቻሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህንን የተናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ማጠቃለያ ላይ ነው፡፡
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት÷ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በርካታ የመኪና ማቆሚያ ተርሚናሎች መገንባታቸውን በማንሳት እነዚህ ተርሚናሎች ከ163 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የማቆም አቅም እንዳላቸዉ ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ ያስባሏት የመንገድ መብራቶቿ መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ በዚህም ጠባብ መንገዶች መስፋታቸውን እና አዳዲስ መንገዶችም መገንባታቸውን ገልጸዋል፡፡ መንገዶች ሲገነቡ ሰፊ መደረጋቸዉ እና የእግረኛ መንገድ ከተሽከርካሪ መለየቱ ሲያጋጥሙ የነበሩ የትራፊክ አደጋ ክስተቶችን መቀነስ እንደቻሉም አብራርተዋል፡፡
ጨለማ የነበሩ መንገዶች ላይ የመንገድ መብራቶች መኖራቸውና የመኪና ማቆሚያዎች በስፋት መሰራታቸው የትራፊክ አደጋን እንዲቀንስ አግዘዋል። ከዚህ በፊት ጨለማ የነበሩ መንገዶችና አካባቢዎች ለስርቆትና፣ ለንጥቂያ እንዲሁም ለጾታዊ ጥቃቶች ሽፋን እንደነበሩ ከንቲባዋ አስታውሰዋል፡፡
የታክሲ እና አውቶብስ ማቆሚያን ከ52 ወደ 603 ማድረስ ተችሏል ያሉት ከንቲባዋ÷ ይሄም የነዋሪዎችን ምቾት የሚጨምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ማእከላት መገንባታቸውንም በማንሳት በየቦታው መጸዳጃ ቤቶች እንዲኖሩ ተደርጓል ነዉ ያሉት።

የደረቅ ቆሻሻ እና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ከተቻለ ከተማን ማሳደግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ በአዲስ አበባ በደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ላይ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ጠቅሰው 1 የነበረውን የፍሳሽ ማጣሪያ ወደ 43 ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ለጤና ስጋት የነበሩ አከባቢዎችን ወደ ምቹ የመዝናኛ ቦታነት መቀየር መቻሉንም ጨምረዉ ተናግረዋል።
በየሻምበል ምሕረት