AMN ሚያዝያ 22/ 2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ራስን በምግብ ለመቻል የነደፈችው ስትራቴጂካዊ ፖሊሲ ዛሬም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት የማሸጋገር ተከታታይ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። ይህ ለዘመናት በጠባቂነት ተገድቦ የነበረው ግዙፍ የሰው ኃይል፣ ወደ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት የሚያደርገው ሽግግር በአስተማማኝ መሰረት ላይ ሆኖ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ዛሬ የጀመርነው የፖሊሲ ስኬት፣ የነገዋን በምግብ ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን እውን የሚያደርግ እየተፋጠነ ያለ የታሪክ ሂደት ነው።
ለዚህ ስኬት መሠረት የሆነው ዋነኛው እርምጃ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲን በቁርጠኝነት ገቢራዊ ማድረግ መቻላችን ሲሆን በዚህም ቀደም ሲል የነበረውንና በዕርዳታ ላይ የተንጠለጠለውን ጠባቂ መዋቅር በመሰበር ትኩረታችንን በሀገር ውስጥ ምርታማነት ላይ አድርገናል ።
በተለይም በግብርናው ዘርፍ የተከተልነው የክላስተር ግብርና እና የመስኖ ስንዴ ልማት ፖሊሲ አርሶ አደሩ በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ እንዲያመርት በማስቻል ፣ የምግብ ዋስትናን ከቤተሰብ እስከ ሀገር ደረጃ እንዲረጋገጥ እልህ አስጨራሽ ትግሎችን አድረገናል። በዚህም ኢትዮጵያን ከስንዴ ተረጂነት አውጥቶ ወደ ስንዴ ላኪነት ያሸጋገረ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ገልጠናል።

ሌላውና ስትራቴጂካዊው ስኬታችን፣ የሴፍቲኔት ፖሊሲያችንን ከመደበኛ የድጋፍ ማዕቀፍ ወደ ንቁ የልማት ተሳትፎ የማሸጋገር ሂደት ነው። መንግሥት ተረጂነትን እንደ ቋሚ አማራጭ የሚወስደውን ነባርና አሰልቺ አካሄድ በመቀየር፣ ዜጎች በልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፉ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ ተከታታይ የፖሊሲ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ይህም ዕርዳታ ለችግር ጊዜ ብቻ የሚውል እንጂ ለኑሮ መሰረት መሆን እንደሌለበት የሚገልጽ አዲስ ብሔራዊ ግንዛቤ እየፈጠረ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችንም በሥራቸው ውጤት ከጥገኝነት አረንቋ ወጥተው ወደ አምራችነት የሚሸጋገሩበት ተለዋዋጭና ቀጣይነት ያለው ሂደት ተፈጥሯል።

ኢትዮጵያ ከተረጂነት ቀንበር ለመላቀቅ የጀመረችው ታላቅ ስትራቴጂ፣ ዛሬ በተጨባጭ የሚታይ ሂደታዊ ስኬት ሆኖ ቀጥሏል። ፖሊሲን ከመሬት ጠብ ከማይል ተግባራዊ ቁርጠኝነት ጋር በማስተሳሰር፣ የተረጂነትን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል። እንደ ሌማት ትርፋት እና ‘የአረንጓዴ አሻራ ያሉ ንቅናቄዎች በተለመደው ቢሮክራሲያዊ አሰራር ሳይገደቡ፣ በከፍተኛ አመራሩ ልዩ ትኩረትና ቀጥተኛ አመራር ወደ ውጤት እየተተረጎሙ ይገኛሉ። ይህ ሂደት የፖሊሲዎቻችንን መሬት የመርገጥ አቅም ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ፣ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ ይበልጥ እያፋጠነው ይገኛል።
ይህ የኢትዮጵያ ስኬት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያስተላልፈው ትልቅ መልዕክት፣ ሀገራችን በራሷ ፖሊሲና በልጆቿ ጥረት የታሪኳን ምዕራፍ እየቀየረች መሆኗን ነው። ዛሬ ተረጂነት በታሪካዊ የልማት ድል እየተተካ፣ የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ በተግባር እየተረጋገጠ ይገኛል።
ሚያዝያ 22/ 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት