በአፍሪካ ውስጥ በፍጥነት እያደገ ያለው የማውንቴን ባይክ ስፖርት ውድድር

You are currently viewing በአፍሪካ ውስጥ በፍጥነት እያደገ ያለው የማውንቴን ባይክ ስፖርት ውድድር

AMN – ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም

በአፍሪካ ወስጥ በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ የስፖርት አይነቶች አንዱ የማውንቴን ባይክ ስፖርት ውድድር ነው፡፡

በርካታ የአፍሪካ ከተሞች እና አካባቢዎቻቸው ለአስቸጋሪ መልክአ ምድራዊ አቀማመጣቸው እና ለተፈጥሮ ውበታቸው ምስጋና ይግባውና የዓለም አቀፍ ውድድሮች መዳረሻ እየሆኑ መጥተዋል፡

በአፍሪካ በስፋት ከሚታወቁ የውድድር መዳረሻዎች መካከል ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚዋ ስትሆን የአፍሪካ የማውንቴን ባይክ ዋና ከተማ ትባላለች፡፡ በተለይም የኬፕ ታውን ተራራማ አካባቢዎች ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ምቹ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ እና ሞሮኮ ማውንቴን ባይክን እንደ ስፖርት ብቻ ሳይሆን እንደ ስፖርታዊ ቱሪዝም በስፋት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በዚህ ውድድር ላይ የዓለም ምርጥ ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል፡፡

በኢትዮጵያ የማውንቴን ባይክ ውድድር እንደ ጐዳና ብስክሌት ባይስፋፋም፣ እንደ እንጦጦ ፓርክ ያሉ ቦታዎች ለልምምድ እና ውድድሮች መነቃቃትን እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች የተገነቡት መሰረተ ልማቶች ለጎዳና ላይ ብስክሌት ጉዞ እና ዉድድር ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል፡፡

የተለያዩ የብስክሌት ውድድሮች በከተማ እና በተራራማ አካቢዎች ጭምር የሚካሄዱ ሲሆኑ ተወዳዳሪዎቹ በጠባብ መንገዶች፣ በደረጃዎች እና በተለያዩ መዝለያ ቦታ ላይ ይሽቀዳደማ፡፡

ከተማው ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች ተፈጥሯዊ ተራራ ባይኖርም፣ አዘጋጆቹ የእንጨት ድልድዮችን፣ የድንጋይ ክምሮችን እና ሌሎች መሰናክሎችን በመንገዱ ላይ ያዘጋጃሉ፡፡

ውድድሩ በከተማ ውስጥ ስለሚከናወን ፣ በርካታ ህዝብ በቀላሉ ሊመለከተውና ሊዝናናበት ይችላል፡፡

የብስክሌት ውድድር በዓለም የብስክሌት ማህበር እውቅና የተሰጠዉ ሲሆን፣ እንደ ባርሴሎናና ፓሪስ ባሉ ትላልቅ ከተሞች በስፋት ይካሄዳል፡፡

ተወዳዳሪዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ፍጥነት የመጨመር ብቃት፤ጠባብ መታጠፊያዎችን እና መሰናክሎችን የመዝለል ጥበብ እና በከፍተኛ ፍጥነት በደረጃዎች እና በኮንክሪት መንገዶች ላይ የመሽከርከር ድፍረት አላቸዉ፡፡

በተራራ ላይ የሚደረጉ የብስክሌት ውድድሮችን ወደ ከተማ በማምጣት ስፖርቱን ለሰዎች ይበልጥ ተደራሽ እና አዝናኝ ማድረግ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ35 የዓለም ሀገራት የሚመጡ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበትን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ከተሞች የማውንቴን ባይክ የሳይክል ውድድርን በአዲስ አበባ ታስተናግዳለች፡፡

ውድድሩ ሚያዝያ 24 እና 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን ውድድሩ በአዲስ አበባ መዘጋጀቱ የመዲናዋን ብሎም የሃገሪቱን የቱሪዝም መስህቦችን እና መልካም ገጽታ በማስተዋወቅ ረገድ የሚኖረዉ ጠቀሜታ የላቀ ነው፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review