የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት የአቶ ሰለሞን ዲባባን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚነት ሹመት አፀደቀ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት የአቶ ሰለሞን ዲባባን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚነት ሹመት አፀደቀ

AMN-ሚያዚያ 30/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ፣ የአቶ ሰለሞን ዲባባ ሚኮን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሹመት አፅድቋል።

ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቀረበለትን ሹመት ያፀደቀው ግለሰቡ በሚዲያ አመራር፣ በስትራቴጂካዊ ኮሙኒኬሽን እና በተቋማዊ ግንባታ ዘርፍ ያላቸውን የላቀ ብቃት እንዲሁም ለከተማዋ ሚዲያ እድገት ያበረከቱትን ጉልህ አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

አቶ ሰለሞን ዲባባ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጆርናሊዝም እና ኮሚዩኒኬሽን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙ ሲሆኑ፣ በዘርፉ ከ12 ዓመታት በላይ ሰፊ የሥራ ልምድ ያካበቱ ባለሙያ ናቸው። ከትውልድ ስፍራቸው ሰሜን ሸዋ ቅምቢቢት ወረዳ ተነስተው በተለያዩ የመንግሥትና የሚዲያ ተቋማት ውስጥ የጎላ አሻራ ማሳረፍ የቻሉ መሆናቸው በጉባኤው ላይ ተጠቅሷል።

አቶ ሰለሞን ቀደም ሲል በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የቴሌቪዥን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የአሁኑ ሹመት እስከተሰጣቸው ድረስም በተቋሙ የዲጂታል ሚዲያ እና ህትመት ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ በመሆን በማገልገል ላይ ነበሩ።

በተጨማሪም አቶ ሰለሞን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊነት፣ በኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ቡድን መሪነት እንዲሁም በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር የኮሚኒኬሽን ኃላፊ በመሆንም በዘርፉ ከፍተኛ የአመራርነት ልምድ አካብተዋል።

በሙያቸውም ከሀገር ውስጥ ተሞክሯቸው በተጨማሪ ስመጥር በሆኑ አለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት መድረኮች ላይ የይዘት ሥራዎቻቸውን ተደራሽ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ይሄም ተቋሙን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግና የአዲስ አበባን ድምፅ ለዓለም ለማድረስ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

በህትመት፣ በምስል እና በዲጂታል ሚዲያው ዘርፍ ያላቸው ሁለገብ ጋዜጠኝነትም ለተቋሙ ሁለንተናዊ ለውጥ እና ሽግግር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል።

አቶ ሰለሞን ዲባባ የሚዲያ ተቋማትን በብቃት የመምራት፣ የለውጥ አቅጣጫዎችን የመቀየስ እና የሚዲያ ስታንዳርዶችን ጠብቆ የመገኘት ልዩ ክህሎት ያላቸው ባለሙያ በመሆናቸው የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ስትራቴጂካዊ ተልዕኮ ለማሳካት ተመራጭ ሆነዋል። ተሿሚው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በታማኝነት ለመወጣት በምክር ቤቱ ፊት ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review