AMN ግንቦት 1/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የተደመረ አቅም ለተቋም ግንባታ!” በሚል መሪ ቃል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ በከተማችን በስድስት ክፍለ ከተሞች የተገነቡ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሕንጻዎችን መርቀን ሥራ አስጀምረናል ብለዋል፡፡
በአዲስ ከተማ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በየካ፣ በቦሌ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች የተገነቡት እነዚህ የፓርቲ ጽሕፈት ቤቶች፤ በአባላትና በደጋፊዎች አስተዋጽኦ፣ እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲ አመራሮችና ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በመለገስ የገነቧቸው ተቋማዊ ሀብቶች ናቸው። በተጨማሪም የፓርቲያችንን ደጋፊዎች በማስተባበር የተገዙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለሁሉም ክፍለ ከተሞች አበርክተናል ብለዋል፡፡

ብልጽግና የያዘውን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ራዕይ ለማሳካትና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት፣ አሰባሳቢ ትርክቶችንና እሳቤዎችን ማስረጽ የሚያስችል ተቋማዊ ግንባታን እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም እየሠራ ይገኛል። ከእሳቤያችን በመነሳት ብዝሃነትን አክብረንና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን አጠናክረን፤ “ከሁሉም፣ በሁሉም፣ ለሁሉም” የሆነች ሀገርን ለመገንባት አሁንም በትጋት እንሠራለን።
ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ መንግሥት መሠረት በመሆኑና ጠንካራ መንግሥት ደግሞ ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ቁልፍ ሚና ስላለው፤ የፓርቲ መዋቅሮቻችንን በየደረጃው የማጠናከር ሥራችንን አጠናክረን ቀጥለናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝባችን ተጨማሪ ዕድል እንዲሰጠን ስንጠይቅ፤ የጀመርናቸውን የሀገረ መንግሥት ግንባታና የአሰባሳቢ ትርክት ሥራዎች ለማጠናቀቅ፣ በሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን ዳር ለማድረስና የሀገራችንን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ ነው።
ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ የሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠበት፣ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን እንፈልጋለን። ለዚህም ስኬት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና አባላት በትኩረት እንዲሠሩ አደራ እላለሁ። ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ አካላት ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡