AMN – ግንቦት 27/2018 ዓ.ም

የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ያዘጋጀውን የመጀመሪያ ደረጃ ምልከታ ሪፖርት ይፋ አድረጓል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎች በምርጫው ወቅት የምርጫ አጀንዳቸውን ለኅብረተሰቡ ማስተዋወቅ እንዲችሉ ሰፊ የሚዲያ ዕድል መመቻቸቱን በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ታዛቢ ቡድኑ በሪፖርቱ በተለይም በሚዲያ ተደራሽነት፣ በአየር ሰዓት ክፍፍል እና በባለድርሻ አካላት ቅንጅት ዙሪያ የታዩ አዎንታዊ እርምጃዎችን በዝርዝር አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ቴሌቪዥንን፣ ሬዲዮን፣ ሕትመትንና ሁለገብ ቋንቋዎችን የሚጠቀሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥርጭት መድረኮችን ባካተተ ግልጽ የዕጣ ሥርዓት አማካኝነት ነፃ የቅስቀሳ አየር ሰዓት እና የዓምድ ክፍፍል መደረጉን አመላክቷል።
በዚሁ መሠረት ነፃ የቅስቀሳ አየር ሰዓቱ ለ66 የስርጭት ጣቢያዎች እና የሕትመት ውጤቶች የተከፋፈለ መሆኑን እና 24 የሬዲዮ ጣቢያዎች በአጠቃላይ 782 ሰዓታትን ለቅስቀሳ ማሰራጨት መቻላቸውን፣ 20 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች 570 ሰዓታትን ለዚሁ ተግባር መመደባቸዉን ገልጿል፡፡
6 ጋዜጦች 576 የዜና ዓምዶችን ለዕጩዎችና ፓርቲዎች ሰጥተዋል።
16 ንዑሳን/ተባባሪ ጣቢያዎች በተለያዩ ቋንቋዎች የሚደረጉ ሥርጭቶች እንዲመቻቹ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸዉንም ጨምሮ ገልጿል፡፡
የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በሪፖርቱ ሌላው በበጎ ጎኑ ያነሳው ነጥብ በምርጫው ሂደት ላይ በተሳተፉ አካላት መካከል የነበረውን ጠንካራ ቅንጅት ነው።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ በሚዲያ ባለድርሻ አካላት እና በደኅንነት ተቋማት መካከል የተደረገው መደበኛ ግንኙነት የተቀናጀ የምርጫ ዝግጅት እንዲኖር ማስቻሉ ተገልጿል።
ይህ ዓይነቱ መደበኛ ምክክርና መስተጋብር በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የተሻሻለና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በፍሬሕይወት ብርሃኑ