የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙስና እና በብክነት ላይ ጥብቅ እርምጃ እየወሰደ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙስና እና በብክነት ላይ ጥብቅ እርምጃ እየወሰደ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ግንቦት 1/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ የምክር ቤት አባላት ከህዝብ ጋር ወርደው ባደረጉት ውይይት መሠረት አባላቱ ምላሽና ማብራሪያ የሚሹ ቁልፍ ጉዳዮችንና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት በማንሳት ተወያይተዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት ሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማ አስተዳደሩ ሙስናና ብልሹ አሰራርን እንደማይታገስ አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በዘንድሮው ዓመት ብቻ በሙስና እና በተለያዩ የአሰራር ግድፈቶች ሳቢያ 420 ያህል ግለሰቦች ተጠያቂ መደረጋቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።

ከተጠያቂዎቹ መካከል እንደ ቤቶች ኮርፖሬሽን እና ቄራዎች ካሉ ተቋማት በተጨማሪ፣ እስከ ዋና መሥሪያ ቤት የመሬት ምክትል ቢሮ ኃላፊ ድረስ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገኙበትና በአንዳንዶቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን፣ የቀሪዎቹ ጉዳይ ደግሞ በፍርድ ቤት በክርክር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

“ተጠያቂነት አይረጋገጥም” የሚባለው ወሬ የተሳሳተ ግንዛቤ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፣ አስተዳደሩ መረጃ ባገኘበት እና በህግ ለመጠየቅ የሚያስችል በቂ ጥርጣሬ ባለበት ሁኔታ በማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይል አረጋግጠዋል።

መንግስት ባደረገው ጥብቅ ቁጥጥር አስተዳደራዊ ወጪዎችን በመቀነስ ከዓመታዊ በጀቱ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማዋል የተቻለ ሲሆን፣ ይህም በከተማዋ ለሚታየው ፈጣን የልማት ለውጥ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ማህበረሰቡ መረጃ በመስጠት፣ ጥቆማ በማቅረብ እና ምስክር በመሆን ለተጠያቂነት መስፈን እያደረገ ያለው ድጋፍም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በግልፅነት እና በቁርጠኝነት በሚመራ የአሰራር ስርዓት ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና የጀመሩትን የልማት አቢዮት አጠናክረው ለመቀጠል በትጋት እየተሠራ እንደሚገኝ በምላሽና ማብራሪያቸው አንስተዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review