የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የዜጎችን ሕይወት እንዴት ቀየረው?

You are currently viewing የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የዜጎችን ሕይወት እንዴት ቀየረው?

AMN – ግንቦት 3/2018 ዓ.ም

ባለቤታቸውን በሞት ሲነጠቁ ዓለማቸው የጨለመች፣ የኑሮ ጫናውና የልጆች እንክብካቤው ግራ ያጋባቸው አቶ ዓለሙ ደሜ፤ ዛሬ ግን በደስታና በተስፋ ይናገራሉ።

ያ በቃላት የማይገለጽ የጭንቀትና የመከራ ወቅት አልፎ፣ ዛሬ ልጃቸው መቆያ ማግኘቱ ለሳቸው “የአእምሮ ነፃነት” ሰጥቷቸዋል። አቶ ዓለሙ ለልጃቸው እናትም አባትም ሆነው ለመገኘት ቢታገሉም፣ ስራና የልጅ እንክብካቤን ጎን ለጎን ማስኬድ ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸው ነበር።

ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘረጋው “የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም” የሕይወታቸውን አቅጣጫ ቀይሮታል።

“መንግስት ድጋፍ አድርጎልኝ ልጄን በዚህ ማዕከል የማስገባት ዕድል ሳገኝ፣ ከትከሻዬ ላይ ትልቅ ሸክም እንደወረደልኝ ተሰማኝ። ልጄን በአስተማማኝ ቦታ ማስቀመጥ መቻሌ፣ በነፃነት ወደ ስራዬ እንድመለስ አስቻለኝ” ይላሉ አቶ ዓለሙ።

ልጃቸው በማዕከሉ የሦስት ዓመት ቆይታው ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ የሚገልጹት አቶ ዓለሙ ቀደም ሲል በቤት ውስጥ ሊያገኝ የማይችላቸውን አልሚ ምግቦች በማዕከሉ በማግኘቱ፣ በአካላዊ እድገቱ ላይ አስደናቂ ለውጥ ታይቷል ብለዋል፡፡

ከሌሎች ልጆች ጋር መጫወቱና የሚሰጠው ትምህርት አእምሮው እንዲከፈትና ንቁ ልጅ እንዲሆን እንደረዳው እና ፍቅሩን የሚገልጽና በንፅህና የሚያድግ ልጅ በመሆኑ፣ አቶ ዓለሙ ስራቸውን በሙሉ ልብና በደስታ እንዲሰሩ ዋስትና ሆኖላቸዋል።

ይህንን ጥራት ያለው አገልግሎት ያለምንም ክፍያ ማግኘት መቻላቸውን እንደ ትልቅ በረከት ይቆጥሩታል። “ለዚህ ታላቅ ተግባር መንግስትንና ከንቲባዋን ከልብ አመሰግናለሁ” የሚሉት አቶ ዓለሙ፣ ዛሬ እርሳቸውም ሆኑ ልጃቸው ነገን በተስፋ የሚመለከቱ አዲስ ሰዎች መሆናቸውን በፈገግታ ገልጸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review