ለሕጻናት ዕድገትና ክብካቤ ተመራጭ የሆኑ የዓለም ሃገራት እና ተሞክሮዎቻቸዉ

You are currently viewing ለሕጻናት ዕድገትና ክብካቤ ተመራጭ የሆኑ የዓለም ሃገራት እና ተሞክሮዎቻቸዉ

AMN- ግንቦት 5/2018 ዓ.ም

ሕጻናት የነገ ሃገር ተረካቢ ትዉልድ እንደመሆናቸዉ መጠን የተመጣጠነ ምግብ እና መልካም ሥነ ምግባር ተላብሰዉ እንዲያድጉ ማድረግ ትልቅ ትኩረት የተሰጠዉ ተግባር ነዉ፡፡

በዓለም ላይ በርካታ ሃገራት ለህጻናት እድገት፣ ደህንነት እና እንክብካቤ የሚያግዙ ፖሊሲዎችን ያወጡ ሲሆን ፖሊሲዎቻቸዉም በአብዛኛዉ በትምህርት፣ በጤና፣ በደህንነት እና በቤተሰብ ድጋፍ ላይ ያኮሩ ናቸዉ፡፡

አይስላንድ ለህጻናት ደህንነት በጣም አስተማማኝ ከሆኑ የዓለም አገራት አንዷ ነች፡፡ ጠንካራ የህጻናት መብት ጥበቃ ህግጋት ያሏት ሲሆን፣ ወላጆች ለልጆቻቸው በቂ ጊዜ እንዲሰጡ የሚያስችል ረጅም የወላጅነት ፈቃድ በመስጠት ትታወቃለች፡፡

ዴንማርክም የህጻናት ክብካቤ ስርዓትን የገነባች ሲሆን በመንግስት ድጎማ ስለሚደረግለት አገልግሎቱን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ማድረግ ችላለች፡፡ በተለይ ህጻናት በነጻነት እንዲጫወቱ እና ማህበራዊ ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስችል የትምህርት ስርዓት ገንብታለች፡፡

ኖርዌይ በበኩሏ ለህጻናት ጤና እና እድገት ከፍተኛ በጀት የምታፈስ አገር ናት። ህጻናት ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው እንዲያድጉ የሚያበረታታ ባህልና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት ታደርጋለች።

ፊንላንድ፤ ኔዘርላንድና ስዊድንን የመሳሰሉ ሃገራትም ለሕጻናት ዕድገትና ክብካቤ የተለየ ትኩረት የሚሠጡ ሃገራት ሲሆኑ፣ ሃገራቱ የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎችን፣ ቤተ መጻህፍትን እና የተለያዩ የመዝናኛ አማራጮችን ለዜጎቻቸዉ ተደራሽ አድርገዋል፡፡

ሃገራቱ ለዚህ ስኬት የበቁት ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎት፤ ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት ፤ የወላጅ ድጋፍ እና ደህንነት በመዘርጋታቸዉ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ኢትዮጵያም በአፍሪካ ለህጻናት እድገትና ክብካቤ ልዩ ትኩረት ከሚሰጡ ሃገራት መካከል ቀዳሚዋ ስትሆን በተለይ ከለዉጡ ሀኋላ ህጻናት በአካባቢያቸዉ የቅድመ መደበኛ ትምህርት አገልግሎት፤ ቤተመጻህፍት፤ የምገባና የትምህርት መርጃ መሳያዎች፤ የመጫወቻና መዝናኛ ስፍራዎች እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በ2015 ዓ.ም በከንቲባ አዳነች አቤቤ መሪነት የተጀመረዉ “አዲስ አበባን ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ የአፍሪካ ከተማ የማድረግ ህልም “ ከስድስት ዓመት በታች የሆኑ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሕፃናት ተገቢዉን የጤና እንክብካቤ፣ ትምህርት እና ሁሉን-አቀፍ አገልግሎት ድጋፍ እንዲያገኙ ባለብዙ ዘርፍ ፕሮግራም ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምም ከ330 ሺህ ለሚበልጡ በኢኮኖሚ ተጋላጭ ለሆኑ ቤተሰቦች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በ2015 ዓ.ም 11 ብቻ የነበረዉን የህዝብ የሕፃናት ማቆያን በ2018 ወደ 1ሺህ 100 በማሳደግ የምግብ፣ የህክምና፣ የስነ ልቦና የእንክብካቤ አገልግሎት በነፃ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በ2015 ዓ.ም 20 ብቻ የነበረዉን የልጆች መጫወቻ በ2018 ወደ 5 ሺህ በማሳደግ ልጆች ቦርቀዉ የሚያድጉበት አካባቢን መፍጠር ተችሏል፡፡

በዚህም አዲስ አበባ ለሕጻናት የምትመች ከተማ ለመሆን የበቃች ሲሆን በርካታ የአፍሪካ ሃገራተም ይህንኑ ተሞክሮ በመቀመር ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review