የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከፍተኛ ደረጃ ውይይት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

You are currently viewing የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከፍተኛ ደረጃ ውይይት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

AMN- ግንቦት 5/2018 ዓ.ም

10ኛው የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከፍተኛ ደረጃ ውይይት ዛሬ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይደረጋል።

በውይይቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደሚገኙ ይጠበቃል።

ውይይቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል በአፍሪካ ልማት እና በዓለም አቀፍ አስተዳደር ዙሪያ ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከርን ያለመ ነው።

በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለውን ቅንጅት፣ የጋራ ተጠያቂነትና ትብብርን በልማት፣ በአስተዳደር፣ በሰብአዊ ድጋፍ እና በሰላም ግንባታ እንዲሁም ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ያላቸውን ትስስር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳል።

በዚህ የከፍተኛ ደረጃ ውይይት ላይ በርካታ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱ ሲሆን፣ በተለይም የአጀንዳ 2063 እና ሁለተኛው የአስር ዓመት ምዕራፍ የትግበራ ዕቅድ አፈፃፀምን ማፋጠን እንዲሁም የአፍሪካን በዓለም አቀፍ ፖሊሲ እና አስተዳደር ውስጥ ያላትን ማዕከላዊ ሚና መጠበቅ በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል።

በተጨማሪም “ከጥገኝነት ወደ ሉዓላዊነት” የተሸጋገረ የልማት ፋይናንስ፣ የ2026 የአፍሪካ ሕብረት የዓመቱ መሪ ቃል የሆነው ዘላቂ የውሃ አቅርቦት እና የፅዳት አጠባበቅ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፎርም እና አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ያላትን ውክልና የተመለከቱ ጉዳዮች ውይይት ይደረግባቸዋል።

መድረኩ ለአህጉራዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ማምጣት፣ የሀገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብን ማሳደግ፣ የወጣቶችና የሴቶች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁም በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ የልማት የቅድሚያ ትኩረቶች መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ወሳኝ መሆኑ አጽንኦት የሚሰጥበት እንደሆነ ተመላክቷል።

ከውይይቱ የሚጠበቁ ውጤቶች መካከል የተሻለ ስትራቴጂካዊ ቅንጅት፣ ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ለውጥ፣ በአፍሪካ ህብረት የዓመቱ መሪ ቃል ዙሪያ ጠንካራ ቅንጅት መፍጠርና በተባበሩት መንግሥታት ሥርዓት ውስጥ ፍትሐዊ የአፍሪካ ውክልና እንዲኖር የቀረቡ ጥሪዎችን ማጠናከር እንደሚገኙበት ኢዜአ ዘግቧል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የውይይቱን ውጤቶች አስመልክቶ የጋራ መግለጫ ይሰጣሉ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review