አዲስ አበባ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን ከከተማ ፕላንና ልማት ጋር በማቀናጀት መተግበሯ በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው

You are currently viewing አዲስ አበባ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን ከከተማ ፕላንና ልማት ጋር በማቀናጀት መተግበሯ በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው

AMN ግንቦት 6/2018

አዲስ አበባ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን ከከተማ ፕላንና ልማት ጋር በማቀናጀት መተግበሯ በአርዓያነት የሚጠቀስ አስደናቂ ተግባር ነው ሲሉ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎች ግንባታ ለሌሎች የዓለም ከተሞች አርዓያ የሚሆኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

አዲስ ዓለምአቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ “አፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ሥርዓት ለውጥ የግንባር ቀደምትነት ሚና፤ ከአካባቢያዊ ሞዴሎች ወደ ዓለምአቀፍ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል፡፡

በዚህም ከፅንስ እስከ ስድስት ዓመት የዕድሜ ክልል የሚደረግ ስኬታማ ኢንቨስትመንት አዲስ አበባን የአፍሪካ ተመራጭ የህፃናት ማሳደጊያ ከተማ እያደረጋት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በአዲስ አባባ እየተከናወነ ያለውን የቀዳማይ ልጅነት ልማት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች፤ ከተማዋ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ከከተማ ፕላንና ልማት ጋር አስተሳስራ እየሰራች ያለችበት መንገድ አስደናቂ ነው፡፡

በፈረንሣይ ሬንስ ዩኒቨርሲቲ የወላጆች አዕምሮ ተመራማሪ ጆዲ ፓውሉስኪ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ እየተተገበሩ ያሉ ፈጣን የልማት ስራዎች የከተማ እድገት ለህፃናት ደህንነትና ለጤና አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን እንዴት ማካተት እንዳለበት የሚያሳይ ትልቅ ምሳሌ ናቸው፡፡

ከተማዋ ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን፣ አረንጓዴ ቦታዎችንና የመጫወቻ ስፍራዎችን በማስፋፋት በኩል ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለችም ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review