AMN- ግንቦት 10/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ፕሮግራምን በይፋ ከመጀመሩ በተለይም ከ2012 ዓ.ም በፊት የምግብ እጥረት በተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
የምገባ ፕሮግራሙ በስፋት ከመጀመሩ በፊት፣ በከተማዋ በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነበር።
በወቅቱ በነበረው ጥናት መሰረት፣ በምግብ እጥረት እና በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ብቻ በየዓመቱ ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ያቋርጡ እንደነበር ነው የሚያመላክተው፡፡
ብዙ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ቢመጡም፣ በምግብ እጥረት ምክንያት በትምህርታቸው ላይ ማተኮር ባለመቻላቸው በትምህርት ዓመቱ አጋማሽ ላይ ትምህርታቸውን የመተው ዝንባሌያቸው ሰፊ እንደነበር ተመላክቷል፡፡

ለአብነትም በ2011/12 ዓ.ም አካባቢ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ በከተማዋ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች በምግብ እጥረት ምክንያት በትምህርት ክፍለ ጊዜ ላይ ራሳቸውን ስተው የሚወድቁባቸው አጋጣሚዎች በብዛት ይመዘገቡ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል የተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እና የትምህርት ቢሮ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፕሮግራሙ ምግብ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ተጨማሪ ዓላማዎችን ሰንቆ የተነሳ ነው።
የመጀመሪያውና ዋነኛው ዓላማ ተማሪዎች በምግብ ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ በማድረግ የነገ አምራች ትውልድን መገንባት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ምግብ የሚያወጡትን ወጪ በመቆጠብ ለሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲያውሉት ለማገዝ ነው።
ሌላው በትውልድ ላይ የሚከሰትን የመቀንጨርና የጤና እክል በመከላከል ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር ያለመ ተግባር ሲሆን፣ በምገባ ማዕከላት ውስጥ በሺዎች ለሚቆጠሩ እናቶችና ወጣቶች ቋሚ የገቢ ምንጭ መፍጠርን ያለመ ፕሮግራም መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ምገባ፣ ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ያገኛሉ።
ይህም በትምህርት ገበታ ላይ የመገኘት ምጣኔንና ውጤታቸውንም በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሸሻለው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሪፖርቶች ያረጋግጣሉ፡፡
በተጨማሪም በ29ኙ የተስፋ ብርሃን ማዕከላት አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና የሀገር ባለውለታዎች በክብር እየተመገቡ ሲሆን፣ ከ30 ሺህ በላይ እናቶች ደግሞ በምግብ አዘጋጅነት ተቀጥረው ቋሚ ገቢ እንዲያገኙ ተደርጓል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚከናወነው የምገባ ፕሮግራም ትኩስ ባህላዊ ምግቦችን በሰፈር እናቶች አማካኝነት በማቅረብ የእናትነት ፍቅርን እና የማህበረሰብ ባለቤትነትን ማረጋጋጡን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ይህ ተግባር ከተማዋ ለምትከተለው ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ፖሊሲ ህያው ማሳያ ነው።
አስማረ መኮንን