AMN – ግንቦት 14/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መገኛ ብቻ አይደለችም፤ የሀገሪቱ ዋና የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የስበት ማዕከልም ጭምር እንጂ።
ይህች መዲና ዛሬ ላይ እንደ ስሟ ውብ አበባን የመሰለ ገጽታን ከመላበሷ በፊት፣ ጉራማይሌ መልክ የነበራት ከተማ መሆኗ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
የአፍሪካን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች፣ ታዋቂ አትሌቶች፣ አርቲስቶች፣ ሙዚቀኞች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የውጭ ሀገራት ዜጎችና ቱሪስቶች ዛሬ ላይ ስለ አዲስ አበባ ልማትና እድገት በአንድ ቃል ይመሰክራሉ።
አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተለውጣለች፣ ዘምናለች፤ ለአፍሪካና ለሌሎች አህጉራት ከተሞችም ምሳሌ መሆን ችላለች።
ከተማዋ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት እንደ ስሟ ውብ አበባ ከመሆኗ በፊት የነበራት ገጽታ፣ ከነዋሪዎቿም ሆነ አዲስ አበባን ከጎበኙ የውጭ ሀገራት ዜጎች እይታ የተሰወረ አይደለም።
አብዛኛው የመዲናዋ ገጽታ በዚህ በኩል ዘመናዊ ህንጻዎች፣ በዚያ ማዶ ደግሞ ያረጁ፣ ያፈጁና የተጎሳቆሉ መንደሮች የሚታዩባት ከተማ ነበረች።
በአንድ በኩል የተንጣለሉ ህንጻዎችና ቪላዎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ፣ በተበጣጠሱ ፕላስቲኮች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች መኖሪያ ሆና ለዓመታት ቆይታለች።
በዚህ በኩል እጅግ ጫፍ በረገጠ የኢኮኖሚ ደረጃ ሁሉም ነገር ተሟልቶላቸው ተደስተውና ተንደላቀው የሚኖሩ ዜጎች የሚኖሩባት፣ በዚያ ማዶ ደግሞ በቆሻሻ መሃል የእለት ጉርሳቸውን ፈልገው የሚኖሩ ወገኖች የሚገኙባት መዲና ነበረች አዲስ አበባ።
የአዲስ አበባ ከተማ እና የነዋሪዎቿ ያለፉት ዓመታት ታሪክ በእነዚህና በሌሎች የኢኮኖሚና የኑሮ ደረጃዎች የሚገለጽ ቢሆንም፣ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ግን ከዘመናዊ ህንጻዎችና ቪላዎች በስተጀርባ በተጎሳቆለና እጅግ መራር በሆነ ሕይወት ውስጥ ስለሚኖሩ ዜጎች ያሰበም ሆነ የተጨነቀ መሪም ሆነ መንግስት አልነበረም።
በዘመናዊ ከተማ መሃል በተጎሳቆሉ የጭቃ ቤቶች፣ ቆርቆሮዎችና ፕላስቲኮች ውስጥ የሚኖሩ የመዲናዋ ነዋሪዎችም፣ ችግሩንም ደስታውንም ችለው ከመኖር ውጪ ይህ የዘመናት የድህነት ታሪክ ይቀየራል የሚል ተስፋ አልነበራቸውም።
እነዚህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ እንዲሁ ‘ነዋሪዎች’ ብቻ ተብለው በቀላሉ የሚገለጹ ሳይሆኑ፣ በአንድ ወቅት ሀገራቸውን በክብር ያገለገሉ፣ ለሀገርና ለወገናቸው ታላቅ ውለታ የዋሉ፣ ወልደው አስተምረው ልጆቻቸውን ለክብር ያበቁ ዜጎች ናቸው።
ድህነት፣ የሰው ልጆች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ አምርረው የሚታገሉት የህይወት ምዕራፍ ቢሆንም፣ እነዚህ ዜጎች ግን በተለያዩ ምክንያቶች ድህነትን ማሸነፍ ተስኗቸው፣ የሰው ልጆችን ክብር በማይመጥን ሕይወት ውስጥ ለዓመታት ለመኖር ተገደው ነበር።
ከረጃጅም ህንጻዎች በስተጀርባ ሆና ስሟ እና ግብሯ ያልተጣጣሙላት አዲስ አበባ፣ ጎዳናዎቿና ወንዞቿ በቆሻሻ የተሞሉ፣ ለአይንም ለአፍንጫም የማይመቹና ዋና የጤና ጠንቅ ነበሩ።
በርካቶች “አዲስ አበባ… አዲስ አበባ…” እያሉ የዘመሩላትና የዘፈኑላት ከተማ፣ ለረጅም ዓመታት ስሟን ከግብሯ ጋር የሚያጣጥምላት ልጅ አጥታ በዚሁ የድህነት ታሪክ ውስጥ ከርማለች።
ከለውጡ ወዲህ ግን በአዲስ አበባ የተከናወኑት በርካታ የልማት አብዮቶች በዘመናዊ ህንጻና ባረጁና ባፈጁ ቤቶች መካከል የነበረውን ጉራማይሌ ገጽታና የመዲናዋን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ የቀየሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ የበርካታ ዜጎችን የኑሮ ሁኔታም ጭምር የለወጡ ናቸው።
በእነዚያ ለሰው ልጆች ክብር በማይመጥኑ ቤቶች ውስጥ ሲኖሩ የነበሩ ዜጎች ዛሬ ላይ በተሻለ ቤት ውስጥ የመኖር ዕድል ማግኘት የጀመሩ ሲሆን፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም በተሻለ ቤትና ሰፈር ከመኖር አልፈው፣ በቀን አንድ ጊዜ ትኩስና ንጹህ ምግብ ከበራፋቸው ላይ ማግኘት ችለዋል።
አንዳንድ የመዲናዋ ባለሀብቶች፣ የግልና የመንግስት ተቋማትም እንደ ትናንቱ ምስኪን ወገኖቻቸውን እያዩ እንዳላየ የሚያልፉ ሳይሆኑ፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም የአቅመ ደካማ ዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚረባረቡ ለመሆን በቅተዋል።
መዲናዋን ብቻ ሳይሆን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት እየቀየረ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ የልማት አብዮት፣ አሁንም ድረስ በድህነት ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ትልቅ ተስፋን ሰንቋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ “አዲስ አበባን እንደ አዲስ” በተሰኘው መጽሐፍ ምረቃ ላይ የመዲናዋን ልማት አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት “አንዳንዶች ልማቱን ስንጀምር ‘አዲስ አበባ ስለማትለወጥ በከንቱ አትድከሙ’ ብለው ሲመክሩን ነበር፤ ነገር ግን አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እና አበባ እናደርጋታለን ብለን ለሕዝባችን በገባነው ቃል መሰረት፣ በፈተና እሳት ውስጥ አልፈን ያቀድነውን ተግብረናል” ሲሉ ተናግረዋል።
በመጽሐፉ ውስጥ የታተሙት ቁጥሮችና ፊደላት የአዲስ አበባን ለውጥ በዝምታ የሚናገሩ ታሪኮች መሆናቸውን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ እያንዳንዱ ገጽ የምኞታችንን ልክ ብቻ ሳይሆን፣ ያንኑ ምኞት መሬት ለማውረድ የለፋነውን ልፋትና የተመዘገበውን ውጤት የሚዘክሩ ናቸው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በወንድማገኝ አሰፋ