መንገድ ላይ ይቆሙ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ወዴት ገቡ?

AMN- ግንቦት 14/2018 ዓ.ም

መኪና ይዞ ወደ አዲስ አበባ እምብርት መውጣትና ደህንነቱ የተጠበቀ ማቆሚያ ማጣት ለዓመታት የአሽከርካሪዎች ዋነኛ የራስ ምታትና ለትራፊክ መጨናነቅ ሰበብ ሆኖ ቆይቷል።

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ጋር ተቀናጅተው የተገነቡት አዳዲስ ዘመናዊ መኪና ማቆሚያዎች ግን ይህንን ታሪክ በከፍተኛ ፍጥነት እየቀየሩት ይገኛሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመላው አዲስ አበባ በተከናወኑት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ለመኪና ማቆሚያዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

አሽከርካሪዎችን ከቦታ ፍለጋ መንከራተት ያዳኑት እነዚህ መሠረተ ልማቶች ፤ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን፣ የሲሲቲቪ ካሜራ ጥበቃንና የአውቶሜትድ አሰራርን በማካተት መዲናዋን ወደ ስማርት ከተማ በማሸጋገር ላይ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል በእግረኛ መንገዶች እና በመንገድ ዳርቻዎች ላይ ያለ አግባብ ይቆሙ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ወደ እነዚህ ዘመናዊ ማቆሚያዎች በመግባታቸው፣ መንገዶች ሰፊና ለእግረኛ ምቹ መሆን ችለዋል።

በመንገድ ዳር የሚደረጉ ህገ-ወጥ ማቆምች ለትራፊክ መጨናነቅና ለአደጋዎች መፈጠር ዋነኛ መንስኤ ነበሩ። መኪናዎች በስርዓት እንዲቆሙ መደረጉ አደጋን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶታል።

በአውቶሜትድ አሰራርና ጥበቃ የሚመሩት እነዚህ ማቆሚያዎች የተሽከርካሪዎች ስርቆትን በከፍተኛ ሁኔታ አስቀርተዋል።

አዳዲሶቹ ማቆሚያዎች በተለየ መልኩ ሁሉም ከቴሌብር እና ከባንክ የዲጂታል ክፍያዎች ጋር የተሳሰሩ መሆናቸው አገልግሎቱን ፈጣንና ከንክኪ ነፃ አድርጎታል።

እነዚህ ስልታዊ ግንባታዎች አዲስ አበባን ወደ ዘመናዊና ስማርት ከተማ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት ማሳያ ናቸው።

የመኪና ማቆሚያ ፍላጎትን መሰረት አድርገው የተዘረጉት እነዚህ መሠረተ ልማቶች ከተማዋን ቀልጣፋና ደህንነቷ የተጠበቀ ዓለም አቀፍ መዲና የማድረግ የሽግግር ሂደት ምሰሶዎች ናቸው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review